ባንግላዴሽ፡ ወሲባዊ ትንኮሳን ሪፖርት በማድረጓ ተቃጥላ የተገደለችው

የፎቶው ባለመብት, family handout
በባንግላዴሽ ኑስራት ጃሃን የተባለች ተማሪ ርዕሰ መምህር ፆታዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት ሪፖርት ማድረጓን ተከትሎ በነጭ ጋዝ አርከፍከው አቃጥለው ገድለዋታል።
የደረሰባትን ትንኮሳ በመናገሯ ድፍረቷን ብዙዎች ቢያደንቁትም ከቀናት በኋላ ግን ሰቅጣጭ የሆነው አገዳደሏ ብዙዎችን አስደንግጧል። ፆታዊ ትንኮሳን ሪፖርት የሚያደርጉ ሰዎች ምን ያህል ለጥቃት ተጋላጭ እንዳደረጋቸውም የሚያሳይ ነው ተብሏል።
በትንሽ መንደር የተወለደችው የአስራ ዘጠኝ አመቷ ኑስራት ማዳራሳ ወይም የእስልምና ትምህርትን ትከታተል ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊትም የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ቢሮው አስጠርቷት በማይሆን መልኩ ሰውነቷን መነካካት ሲጀምር ሮጣ እንደወጣች ተናግራለች።
በባንግላዴሽ በየትኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች በቤተሰብና በማህበረሰቡ ሊደርስባቸውን የሚችለውን መሸማቀቅ በመፍራት ፆታዊ ጥቃቶችን ሪፖርት አያደርጉም።
ኑስራትን ለየት የሚያደርጋት ግን በግልፅ መናገሯ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ እርዳታ ወደ ፖሊስ ሄዳ ሪፖርት ማድረጓ ነበር።
በፖሊስ ጣቢያውም ውስጥ ደህንነቷን በሚያስጠብቅ መልኩ ሳይሆን የተፈፀመባትን ነገር በዝርዝር በምታስረዳበት ወቅት ፖሊሱ በስልኩ እየቀረፃት ነበር።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ እንደሚያሳየው ኑስራት በተጨናነቀ መልኩ በእጇ ፊቷን ለመደበቅ ጥረት ብታደርግም፤ ፖሊሱ ግን የደረሰባትን ጥቃት "ትልቅ ነገር" አይደለም በማለት እጇን ከፊቷ ላይ እንድታነሳ ይነግራት ነበር።
ተንቀሳቃሽ ምስሉም የኃገር ውስጥ ሚዲያዎች እጅ ውስጥ ገብቶ ለህዝብ እይታ በቃ።
'ትምህርት ቤት ልወስዳት ሞክሬ ነበር'

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto/Getty Images
ከወግ አጥባቂ ቤተሰብ የተወለደችው ኑስራት ምንም እንኳን ትንኮሳን ሪፖርት በማድረጓ ከማህበረሰቡ ሊከተላት የሚችለውን ነገር አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም እሷ ግን አይበገሬ ነበረች።
የተለያየ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ከማህበረሰቡ በአካል፣ በተለያዩ ድረገፆች ከቃል ዘለፋ ጀምሮ አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ኑስራትም ከዚህ አላመለጠችም።
ለፖሊስ ሪፖርት ካደረገች በኋላ ርዕሰ መምህሩ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ለኑስራት የከፋ ነበር። ግለሰቡ እንዲለቀቅ የሚጠይቁ ሰዎች ጎዳናውን አጥለቀለቁት።
ተቃውሞውን ያደራጁት ሁለት ወንድ ተማሪዎች ሲሆኑ የአካባቢውም ፖለቲከኞችንም ድጋፍ ማግኘት እንደቻሉ ተገልጿል።
ምንም እንኳን ተጠቂዋ እሷ ብትሆንም ብዙዎች እሷን መወንጀል ጀመሩ። ቤተሰቧም የደህንነቷ ሁኔታ እንዳስጨነቃቸውም መናገራቸው ተዘግቧል።
ጥቃቱን ሪፖርት ካደረገች ከአስራ አንድ ቀናት በኋላ ፈተና ልትፈተን ትምህርት ቤት ሄደች።
"እህቴን ትምህርት ቤት የወሰድኳት እኔ ነኝ። ወደ ግቢው ለመግባት ስጠይቅ እንደማይፈቀድልኝ ነገሩኝ" በማለት የሚናገረው ወንድሟ ማህሙዱል ሃሰን ኖማን " ከመግባት ባያስቆሙኝ ኖሮ እንዲህ አይነት ሰቅጣጭ ጉዳይ በእህቴ ላይ አይፈፀምም ነበር" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Shahadat Hossain
ከመሞቷ በፊት ኑስራት በሰጠችው መግለጫ አንዲት ሴት ተማሪ አንድ ጓደኛዋ እንደተጎዳ ነግራት ጣራው ላይ ወሰደቻት። ጣራው ላይ ስትደርስ ግን አምስት ተማሪዎች እንደከበቧትና በርዕሰ መምህሩ ላይ ያቀረበችውን ክስ እንድትተው ጫና ሊያደርጉባት ሞክረዋል። እምቢ ስትልም በእሳት እንደለኮሷት ተናግራለች።
የወንጀል መርማሪ ፖሊስ ኩማር ማጁምደር እንደገለፀው ገዳዮቿ ራሷን ያጠፋች ለማስመሰል ቢሞከሩም እቅዳቸው ሳይሳካም ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በህይወት ተርፋ መግለጫ መስጠት ችላለች።
"አንደኛዋ ገዳይዋ በእጆቹ ጭንቅላቷን ያስጎነበሳት ሲሆን፤ እጁም እንዳይነካ በሚል ጭንቅላቷ ላይ ነጭ ጋዝ ያላርከፈከፉባት ሲሆን በዚህም ምክንያት ጭንቅላቷ ከመቃጠል መትረፍ ችሏል" በማለት የወንጀል መርማሪው ፖሊስ ኩማር ተናግሯል።
ነገር ግን ኑስራት ወደ አካባቢው ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ ግን 80% ሰውነቷ እንደተቃጠለና ለተሻለም ህክምና ወደ ሌላ ሆስፒታል ተልካለች።
በአምቡላንስ ውስጥ እያለች በህይወት አልኖርም ብላ በመፍራት በወንድሟ ስልክ የደረሰባትን ነገር ቀድታዋለች።
"መምህሩ ነክቶኛል፤ እስከ መጨረሻ እስትንፋሴም ቢሆን የደረሰብኝን ወንጀል እታገላለሁ"ስትልም ተሰምታ ነበር።
ጥቃት ያደረሱባትም ግለሰቦችም እዛው የሚማሩ ተማሪዎች መሆናቸውንም ተናግራ ነበር።
ሆስፒታልም በነበረችበት ጥቂት ቀናትም የባንግላዴሽ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ ሽፋን ሰጥተውት የነበረ ጉዳይ ሲሆን፤ ለቀብሯም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደተወለደችበት መንደር መጥተዋል።
እስካሁን ድረስ ፖሊስ አስራ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ሰባቱ በቀጥታ ከግድያዋ ጋር በተገናኘ ነው። ከነዚህም ውስጥ ለርዕሰ መምህሩ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተቃውሞ ሰልፍ አደራጅተው የነበሩ ሁለቱ ግለሰቦች ይገኙበታል።
ርዕሰ መምህሩ አሁንም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲሆን፤ ኑስራት ለፖሊስ ሪፖርት ስታደርግ ሲቀርፃት የነበረው ፖሊስም ከኃላፊነቱ ተነስቶ ወደ ሌላ ዘርፍ እንደታዛወረ ተዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሀሲና የኑስራትን ቤተሰብ ያገኙዋቸው ሲሆን ጥፋተኞቹ ሁሉ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ቃል ገብተውላቸዋል። "ጥፋተኛ የሆነ ሁሉ ከህግ አያመልጥም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Shahadat Hossain
የኑስራት ሞት ከፍተኛ ተቃውሞን የቀሰቀሰ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችም ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ንዴታቸውን ገልፀዋል።
"ብዙ ልጃገረዶች እንዲህ አይነት ጥቃት ሲደርስባቸው በፍራቻ ምክንያት ተቃውሟቸውን አያሰሙም። መሸፋፈን አይደለም ከብረት የተሰራ ልብስ ደፋሪዎችን አያስቆምም" በማለት አንድ አስተያየት ሰጪ ተናግሯል።
"በህይወቴ ሁሉ የምፈልገው ሴት ልጅ እንድትኖረኝ ነበር፤ ነገር ግን በዚች ሀገር ላይ ሴት ልጅ መውለድ ማለት ጭንቀትና ፍራቻ የተሞላ ህይወት ማለት ነው" በማለት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ገልፃለች።
"ሴቶች የደረሰባቸውን ፆታዊ ትንኮሳ ሪፖርት ማድረግ ማለት ሌላ ትንኮሳን ማስተናገድ ማለት ነው። ጉዳዩ ለአመታት ይንጓተታል፤ ማህበረሰቡ ያሸማቅቃቸዋል። ከፖሊስ በኩል ጉዳዩን ለመርመር ፍቃደኝነት አያሳዩም። ወንጀለኞቹም ሳይቀጡ ይቀራሉ፤ ተጠቂዎቹም ፍትህ አያገኙም" በማለት የሰብአዊ መብት ጠበቃና የቀድሞ የሴቶች የህግ ባለሙያ ማህበር ዳይሬክተር ሳልማ አሊ ተናግረዋል።
ብዙዎችም አሁንም እየጠየቁ ያሉት ጥቃቷ ከሞተች በኋላ ለምን ትኩረት አገኘ? እንዲሁም የሷ ሁኔታ ማህበረሰቡ ፆታዊ ጥቃትን የሚመለከትበትን መንገድ ይቀይረው ይሆን የሚሉ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












