ቦትስዋና ዝሆኖችን መግደል ለሚፈልጉ አዳኞች ጨረታ አወጣች

ዝሆኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቦትስዋና ሰባ ዝሆኖችን ለመግደል እንዲችሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋነኛ የተባለ ጨረታ በማካሄድ ለአዳኞች ፈቃድ ልትሰጥ መሆኑ ተነገረ።

ለዚህም የቦትስዋና መንግሥት በውስጣቸው 10 ዝሆኖችን ለመግደል የሚያስችል ፈቃድ ያላቸው ሰባት ማዕቀፎችን የያዙ የጨረታ ሰነዶችን እየሸጠ ይገኛል።

ዝሆኖቹን ለመግደል ፍላጎት ያላቸው አዳኞች በጨረታው ለመሳተፍ 18 ሺህ ዶላር የጨረታ ማስያዣ ማስቀመጥ አለባቸው።

በዚህ ዓመት የሚኖረው የአደን ወቅት በሚያዚያ ወር የሚጀምር ሲሆን ከዚያ በፊትም ተጨማሪ 200 ዝሆኖችን ለመግደል የሚያስችል የአደን ፈቃድ በወቅቱ እንደሚሰጥም ተነግሯል።

ከስድስት ዓመታት በፊት ቦትስዋና ዝሆኖችን ለመጠበቅ ማንኛውንም አይነት አደን የሚከለክል እገዳ አውጥታ ነበር። ይህም እገዳ እንስሳቱን በመጠበቅ በኩል የስኬት ታሪክ እንደሆነ ተነግሯል።

ነገር ግን እገዳው በአገሪቱ ፕሬዝዳናት ባለፈው ዓመት እንዲነሳ ተደርጓል። በዚህም ሳቢያ ተቺዎች ፕሬዝዳንቱ ዘወትር በዝሆኖች ላይ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡ የገጠር ነዋሪዎችን ለማስደሰትና ድምጻቸውን ለማግኘት የወሰዱት እርምጃ ነው ሲሉ ተቃውመውታል።

የመንግሥት ባለስልጣናት ግን ዝሆኖቹ የአርሶ አደሮችን ሰብል በማውደምና አንዳንድ ጊዜም በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው በሚል ይከራከራሉ።

ቦትስዋና በግዛቷ ውስጥ 130 ሺህ የሚገመቱ ዝሆኖች ያሏት ሲሆን በዓለም ከፍተኛ የዝሆን ቁጥር ያላት ቀዳሚ አገር ናት።