ናይጄሪያ የቪዛ እገዳው እንዲነሳ የትራምፕን ማሻሻያ እቀበላለሁ አለች

ቡሃሪና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሜሪካ ናይጀሪያን ጨምሮ በስድስት አገራት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን ተከትሎ ናይጀሪያ ያለባትን የፀጥታና ደህንነት ክፍተት ለማሻሻል እንደምትሰራ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ አስታውቀዋል።

በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር አንደኛ የሆነችው ናይጄሪያ ከአሜሪካ ጋር "መልካም የሆነ ግንኙነት" እንዲኖራት እንደሚፈልጉም ምኞታቸውን ተናግረዋል።

አዲሱን የቪዛ መስፈርቶች የሚያጠና አንድ ኮሚቴም ያቋቋሙ ሲሆን ለዚህም ሚኒስትር መድበዋል።

ናይጄሪያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ኪርጊዝስታን እና ሚያንማር አሜሪካ ከምትሰጣቸው የተወሰኑ የቪዛ አይነቶችን እንዳያገኙ እገዳ ጥላባቸዋለች።

የእነዚህ አገራት ዜጎች የተወሰኑ አይነት ቪዛዎችን ለማግኘት እንደማይችሉ ቢገለጽም የቱሪስት ቪዛ ግን ለማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

በ2018 አሜሪካ ከስምንት ሺ በላይ ለሚሆኑ ናይጄሪያውያን ቪዛ የሰጠች ሲሆን ይህም ቁጥር አሁን እገዳ ከጣለችባቸው አምስት ሃገራት ካገኙት ቪዛ ከሁለት ዕጥፍ በላይ ነው።

በዚሁ ዓመት አሜሪካ ከ8 ሺህ በላይ ቪዛ ለናይጄሪያዊያን፣ 2 ሺህ ለሱዳናዊያን፣ 290 ለታንዛኒያዊያንና 31 ደግሞ ለኤርትራዊያን ሰጥታለች።

"እነዚህ አገራት በብዙ መልኩ መተባበር ቢፈልጉም ከሃገራቱ የምንፈልገውን ዝቅተኛውን መስፈርት እንኳን ማሟላት ባለመቻላቸው እገዳው አስፈላጊ ሆኗል" በማለት ተጠባባቂ የአገር ውስጥ የደህንነት ሚንስትር ቻድ ዎልፍ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቻድ ዎልፍ አክለውም እገዳ ከተጣለባቸው ሃገራትም ጋር የደህንነትና የፀጥታ መስፈርቱን የሚያሻሽሉበትን መንገድ ለመቀየስ አብረው እንደሚሰሩ ጠቅሰው በሂደትም ከእገዳ ዝርዝሩ እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።

አዲሱ የአሜሪካ የቪዛ ህግ ተግባራዊ የሚሆነው ከሃያ ቀናት በኋላ ሲሆን ለባለስልጣናት፣ በንግድ ለተሰማሩ ግለሰቦች እንዲሁም የቱሪስት ቪዛን በሚጠይቁ ሰዎች ላይ እንደማይተገበር የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ቢሮ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ አትቷል።

"ናይጄሪያ ከአሜሪካም ሆነ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ማስቀጠል ትፈልጋለች፤ በተለይም በዓለም አቀፍ ደህንነትና ፀጥታ ዙሪያ አንደራደርም" በማለት የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ ፌሚ አዴሲና ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉዞ እገዳ ያደረጉት በ2017 ነው። ያኔ በተረቀቀው መመሪያ መሰረትም ሰባት ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታይ ህዝብ ቁጥር ያላቸው አገራት የአሜሪካን ቪዛ እንዳያገኙ ክልከላ ተደርጎባቸው ይገኛሉ።

አሜሪካ ከዚህ ቀደምም በ2017 ለኤርትራዊያን የተወሰኑ የቪዛ ዓይነቶችን ከልክላ ነበር።

ለመሆኑ አዲሱ መመሪያ ምንድን ነው?

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ከናይጄሪያ፣ ኤርትራ፣ ኪርጊዝስታንና ሚያንማር ለሚመጡ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ይዘት ያለው ቪዛ አይሰጣቸውም።

ታንዛንያና ሱዳን ደግሞ በዲቪ ሎተሪ እንዲሳተፉ አይፈቀድላቸውም።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ለጎብኝዎች፣ የንግድ ሥራ ለሚሰሩና ሕክምና ለሚያደረጉ ሰዎች የሚሰጠው ጊዜያዊ ቪዛ ግን ከእገዳው ጋር እንደማይገናኝ ባለስልጣኑ አረጋግጠዋል።

እገዳው ከተጣለባቸው አገራት መካከል ኪርጊዝስታን እና ሱዳን በአብዛኛው ህዝባቸው የእስልምና ተከታይ ሲሆን፤ ናይጄሪያና ኤርትራ ደግሞ የእስልምና ተከታይ ቁጥር ህዝባቸው አምሳ በመቶ ነው።

የጉዞ እገዳው ምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስልጣን ላይ በወጡ በሰባተኛ ቀናቸው ነበር አወዛጋቢውን የጉዞ እገዳ የሚያትት መመሪያ የፈረሙት። እሳቤው የአሜሪካን ደህንነት ለመጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው በሚል ነበር።

እገዳው ሰባት በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ባላቸው አገራት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ከፍርድ ቤትም ብርቱ ሙግት ገጥሞት ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባረቀቁት አወዛጋቢ መመሪያ መሰረትም የኢራን፣ ሊቢያ፣ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ቬኒዙዌላ እና ሰሜን ኮሪያ የእገዳው ሰለባ ሆነዋል።

ከእነዚህ አገራት ወደ አሜሪካ ለሚመጡ ዜጎች የቪዛ እገዳው ቢጣልም ለተማሪዎችና አለፍ ሲልም ከአሜሪካ ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው ለተባሉ ግለሰቦች እገዳው የተጣለባቸው አገራት ዜጎች ቢሆኑም ቪዛ የማግኘት ልዩ እድል እየተመቻቸላቸው ነው።