በኮሮናቫይረስ ስጋት ናይጄሪያ የቻይናዊያን መደብርን ዘጋች

የፎቶው ባለመብት, FCCPC
የናይጄሪያ ባለስልጣናት በዓለም ዙሪያ በአሳሳቢ ሁኔታ እየተዛመተ ካለው የኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በዋና ከተማዋ አቡጃ የሚገኝ የቻይናዊያን መደብርን ዘጉ።
እርምጃውን የወሰደው የናይጄሪያ ሸማቾች ጥበቃ ተቋም እንዳለው እንዲዘጋ የተደረገው የቻይናዊያን መደብር "በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የዓሳና የሥጋ ምርቶችን ሲሸጥ" በመገኘቱ ነው።
ተቋሙ እርምጃውን የወሰደው እነዚህ ምርቶች የኮሮና ቫይረስን ሊያዛምቱ ይችላሉ በሚል ስጋት እንደሆነም ተገልጿል።
የናይጄሪያ መንግሥት የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ኮሚሽን በሕገወጥ መንገድ የገቡትን የምግብ ምርቶች ሊይዝ የቻለው በመደብሩ ላይ ባደረገው "ድንገተኛ" ፍተሻ መሆኑን ገልጿል።
ተቋሙ ጨምሮ እንዳመለከተው ከሱፐርማርኬቱ ከተያዙት የምግብ ምርቶች መካከል አብዛኞቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ናቸው።
ተቋሙ ስለወሰደው እርምጃ እንደተናገረው በመደብሩ ውስጥም "ለእስያዊያን ተጠቃሚዎች ተብሎ የተዘጋጀ የተለየና ድብቅ ቦታ" ማግኘቱን አመልክቷል።
አክሎም በሕገ ወጥ መንገድ ከቻይና የገቡ የዓሳና የሌሎች እንስሳት ምርቶች ማግኘቱን አረጋግጦ፤ የኮሮናቫይረስን ስርጭትን ግምት ውስጥ በማስገባት መደብሮቹ እንዲዘጉ መደረጉን ገልጿል።
እስካሁን ከ150 በላይ ሰዎችን የገደለውና ወደ ተለያዩ አገራት እየተዛመተ ያለው አዲሱ ኮሮናቫይረስ በቻይናዋ ዉሃን በተባለችው ከተማ ውስጥ በሚገኝ የዓሳ መሸጫ ገበያ ውስጥ እንደተቀሰቀሰ ይነገራል።
የናይጄሪያ ባለስልጣናትም እርምጃ ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ስጋት እንደሆነ ተነግሯል።












