24 ሺህ ፖስታዎችን ማደል የታከተው የዓለማችን ስልቹው ፖስተኛ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሥራው የተሰላቸው ፖስተኛ ማድረስ የነበረበትን በሺዎች የሚቆጠሩ ፖስታዎች ቤቱ ውስጥ ከምሮ በፖሊስ ተያዘ።
በዚህም የጃፓን ፖሊስ በሰውየው ላይ የምርመራ ዶሴ ከፍቶበታል።
ጃፓናዊው ፖስተኛ ሲበዛ ስልቹ ነው። እንዲያደርስ ከተነገረው ፖስታ መሀል 24 ሺህ የሚሆነውን ቤቱ አስቀምጦታል። ክፋት አይደለም መታከት ነው ብሏል።
ይህ ፖስተኛ ከቶኪዮ ወጣ ብላ በምትገኘው ካናጋዋ ቀበሌ ውስጥ በሚገኘው ቤቱ 24 ሺህ የፖስታ ጥቅሎችን ፖሊስ ባገኘበት ቅጽበት ታላቅ መገረምን ፈጥሮ ነበር።
የ61 ዓመቱ ጎልማሳ ፖስተኛ የፖስታ ጥቅሎቹን ለምን አላደልክም ሲባል "ይሰለቻል" ብሏል።
በዚያ ላይ ከእርሱ በዕድሜ የሚያንሱት ፖስተኞች ጋር መወዳደርና ሰነፍ ሆኖ መታየት እንዳልፈለገም ተናግሯል።
የዮኮሃማ ፖስታ ቤት በሰውየው ስንፍና ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን "ችግር የለም ሁሉንም እኔ ራሴ አድላቸዋለሁ" ብሏል።
ይህ ስልቹ ጃፓናዊ በሚሰራበት ፖስታ ቤት ቅርንጫፍ ከ2 ዓመት በፊት ፖስታዎች እየተሰወሩ ነው ምርመራ ይጀመር ብሎ ነበር።
ነገር ግን በኋላ ይፋ የሆነው የፖሊስ ምርመራ እንዳመላከተው ይህ ስልቹ ፖስተኛ ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ ነው ፖስታ ማደል አሰልቺ እንደሆነ ተሰምቶት ቤቱ መከመር የጀመረው።
ይህ በስም ያልተጠቀሰው ጃፓናዊ ስልቹ ፖስተኛ በተከሰሰበት ወንጀል ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ካለው 3 ዓመት እስር እንዲሁም ግማሽ ሚሊዮን የን ሊቀጣ ይችላል። ቅጣቱ ወደ ብር ሲቀየር 150 ሺህ ብር ይጠጋል።












