አውስትራሊያዊቷ ኬክ በፍጥነት በመብላት ውድድር ላይ ሳሉ ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስትራሊያ አንዲት ሴት ብዙ ኬክ በፍጥነት በመብላት ውድድር ላይ ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል።
ሴትየዋ 60 ዓመታቸው ሲሆን በኪውንስላንድ ሃርቬይ ቤይ ውስጥ በሚገኝ ቢች ሃውስ በተባለ ሆቴል ኬክ ቶሎ በልቶ የመጨረስ ውድድር ላይ ሳሉ ነበር ራሳቸውን ስተው የወደቁት።
ተወዳዳሪዎቹ ቀደም ብለው ላሚንግተን የተሰኘውን ከቼኮሌትና ከኮኮነት የተሠራ ኬክ ሲበሉ ነበር።
ሴትዮዋ በወቅቱ የመጀመርያ እርዳታ ተደርጎላቸው ሆስፒታል በፍጥነት የተወሰዱ ቢሆንም ሕይወታቸን ማትረፍ ግን አልተቻለም።
የዐይን እማኞች እንደሚሉት ሴትየዋ በውድድሩ ላይ አንዱን ኬክ ጎርሰው ሌላ ለመድገም ሲሞክሩና ሲታገላቸው እንደነበር መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ኋላ ላይ በወጡ የተንቀሳቃሽ ምሥሎች መረዳት እንደተቻለው በሆቴሉ ውስጥ የተገኙ ጠጪዎች ለተወዳዳሪዎቹ እያጨበጨቡ ድጋፍ ሲሰጡ ነበር።
ተወዳዳሪዎቹ ከሚመገቡት ኬክ በተጨማሪ በብርጭቆ ውሃ ቀርቦላቸው እንደነበረም ተንቀሳቃሽ ምሥሉ መስክሯል።
በሃርቬይ ቤይ የሚገኘው የቢች ሃውስ ሆቴል ፌስቡክ ገጽ ለሴትዮዋ ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል።
በአውስትራሊያ የድል ቀን ምግብ በፍጥነት በልቶ የመጨረስ ውድድር እጅግ የሚዘወተር መዝናኛ ነው።
የአውስትራሊያ የድል ቀን አውሮፓዊያኑ አውስትራሊያ የደረሱበትን ቀን የሚዘክር በዓል ነው።
በዚህ የድል ቀን ተወዳዳሪዎች ሆትዶግ፣ ኬክ፣ ወይም ሌሎች ምግቦችን በፍጥነት ከተመገቡ ዳጎስ ያለ ሽልማትን ያሸንፋሉ።












