የታገቱት 17ቱ ተማሪዎች፡ "ከታገቱት መካከል አንዷ ነበርኩ፤ በሦስተኛ ቀኔ አምልጫለሁ"

ካርታ
የምስሉ መግለጫ, ተማሪዎቹ የታገቱት ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ በሚወስደው መንገድ ላይ ነው

17 የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ በታጣቂዎች ከታገቱ ሳምንታት ተቆጠሩ።

በታጣቂዎች ታግተው ከሚገኙት 17ቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 13ቱ ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን ከአጋቾቹ ካመለጠች ተማሪ ማወቅ ተችሏል።

"ከታገቱት መካከል አንዷ ነበርኩ፤ በሦስተኛ ቀኔ አምልጫለሁ" ተማሪ አስምራ ሹሜ

ተማሪ አስምራ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።

"በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነበርኩ። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በመዘጋቱ ወደ ትውልድ አካባቢዬ ተመልሼ አዲስ ዘመን ከተማ ነው ያለሁት።

ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ። መጀመሪያ በአጋቾቹ የተያዝነው 18 ተማሪዎች ነበርን። እኔ ማምለጥ ስለቻልኩ አሁን ታግተው ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ወንዶች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። አሁን ታግተው ያሉት ተመራቂ ተማሪዎች እና የኢንጅነሪንግ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው።

በወቅቱ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ስለነበር ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተው ነበር። እኛም መውጣት አሰብን ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ የሚያስመጣው ዋና መንገድ በመዘጋቱ ከደምቢ ዶሎ በጋምቤላ በኩል አድርገን አዲስ አበባ ለመግባት ወሰንን።

ሁላችንም ከአማራ ክልል አካባቢዎች የመጣን ተማሪዎች ነን።

ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ የ30 ብር ትራንስፖርት ሲሆን እቅዳችን ጋምቤላ አድረን ወደ አዲስ አበባ ነበር። ነገር ግን ያሰብነው ቦታ ሳንደርስ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል 'ሱድ' የምትባል ቦታ ላይ ስንደርስ መኪናውን አስቁመው፤ ወጠምሻ ወጣቶች መጥተው አፈኑን። የአፋኞቹ ቁጥር ከእኛ ቁጥር በላይ ነበር።

አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።

እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።

በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።

እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ 'የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት' ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።

'ከታየሁ እኔም እገደላለሁ' ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታተላለን' አሉኝ።

ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም 'በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከልክሉናል' ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ 'የእነርሱ ነው ያዥው' ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።

ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። 'እንከታተላለን' ነው ያሉኝ።

ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን 'መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ' እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።"

Presentational grey line

የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ምን ይላሉ?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸውን ለልጆቹ ደህንነት ስንል ያልጠቀስናቸው የታገቱት ተማሪ ቤተሰቦች፤ ተማሪዎቹ ከታገቱ አንድ ወር እንዳለፋቸው ይናገራሉ። "በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ስልክ ይደውሉ ነበር፤ አሁን ግን ድምፃቸውን ከሰማን ሦስት ሳምንታት አልፈዋል" ይላሉ።

እህቱ እንደታገተችበት የነገረን አንድ ግለሰብ፤ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ሲወጡ፤ እርሱም እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ቢነግራቸውም እነርሱ ግን ከአሁን አሁን ይረጋጋል እያሉ መቆየታቸውን ያስረዳል።

ይህ ግለሰብ እንደሚለው ስልክ ተደውሎለት እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ስለመታፈናቸው የሰሙት ሕዳር 24፣ 2012 ዓ.ም ነው።

ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት በተማሪዎቹ ስልክ ከዚያ በኋላ 'የአጋቾቹ ነው' ባሏቸው ስልክ ይደውሉላቸው ነበር። ቦታውን ሲጠይቋቸው ግን እንደማያውቁት ነበር ሲነግሯቸው የቆዩት።

"የሆነ ሰዓት ላይ ስልክ ተሰጥቷት የፅሁፍ መልዕክት ላከችልኝ፤ ''አሻና አፋን ገደራ' የሚባል ቦታ ነው ያለነው፤ ለመከላከያ ደውሉና እዚህ አካባቢ ይፈልጉን' ብላ ፃፈችልኝ" ይላል።

በመጨረሻው የስልክ ልውውጣቸው፤ "አሁንም እዚያው ቦታ ነሽ ወይ?" ብሎ ሲጠይቃት "በፊት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ አሁን ቦታ ቀይረናል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የሁለት የሦስት ሰዓት መንገድ በጫካ እንጓዛለን፤ አታገኙንም፤ አሁንም ልትንቀሳቀሱ ነው ተብለናል፤ እስካሁን ባለው ደህና ነን'' ስትል ስልኩን ከዘጋች ወዲህ እህቱን በስልክ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።

ከታጋች ተማሪዎች ወላጆች መካከል ሁለት ሰዎች፤ ስለ ልጆቻቸው መረጃ ፍለጋ ወደ ደምቢ ዶሎ ተጉዘው እንደነበረ ይሄው እህቱ የታገተችበት ወንድም ይናገራል።

እሱ እንደሚለው ወደ ሥፍራው የሄዱት ሰዎች ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።

ሌላኛዋ የታጋች ተማሪ እህት እንደነገረችን፤ ቀደም ብሎ በዩኒቨርሲቲው አንድ የአማራ ተወላጅ ተማሪ መገደሉን ተከትሎ ወንድሟ ከፍተኛ ስጋት አድሮበት እርሷ ጋር ደውሎ ገንዘብ እንድትልክለት መጠየቁን ታስታውሳለች።

"የደወለው ቅዳሜ ቀን ስለነበር እስከ ሰኞ እንዲታገስ ነገርኩት፤ ሰኞ ዕለት ብር ልልክለት ስደውል ስልኩ አይሰራም። በማግስቱ ደውሎ መያዛቸውን ነገረኝ። ከተያዙ ጀምሮ ሁለት ሳምንታት ድረስ ይደውሉ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ድምፃቸው አልተሰማም" ትላለች።

እስካሁን የምንችለውን ነገር ሁሉ እያደረግን ነው የምትለው የተማሪው እህት፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የምታገኛቸው የታጋች ወላጆች በከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ትናገራለች።

"አንጀታቸውን በገመድ አስረው መሬት ላይ ተኝተው ይፀልያሉ፤ 'ሞተው ከሆነ አስክሬናቸው ይምጣልን'" እያሉ ነጋ ጠባ እያለቀሱ ነው" ትላለች።

ተማሪዎቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸውና እየተሰቃዩ እንደሚገኙ መስማታቸውንም አክላለች።

Presentational grey line

የአጋቾቹ ፍላጎት ምንድነው?

ወንድሟ የታገተባት እህት ከወንድሟ ባገኘችው መረጃ መሠረት አጋቾቹ ገንዘብ አይፈልጉም።

ከአጋቾቹ እጅ ያመለጠችው አስምራ እንደምትናገረው፤ አጋቾቹ በተደጋጋሚ "ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም። ጸባችን ከመንግሥት ጋር ነው" እንደሚሉ ትናገራለች።

አጋቾቹ "የአማራ ሕዝብ ልጆቻችን ታግተዋል ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፤ መንግሥት እኛን ያነጋግራል። የዛኔ እኛ ጥያቄያችንን ለመንግሥት እናቀርባለን፤ ጥያቄያችንም ይመለሳል" እንዳሉ አስምራ ገልፃልናለች።

የመንግሥት አካላት ምላሽ?

ኦሮሚያ

የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ "ምንም አይነት መረጃ የለኝም። እኔ የሰማሁት ነገር የለም" ይላሉ።

ጉዳዩ እርሳቸው የሚመሩትን ቢሮ በቀጥታ የሚመለከት መሆኑን በመጥቀስ ስለጉዳይ እንዴት መረጃ ሳይኖራቸው እንደቀረ የተጠየቁት ኮሎኔል አበበ ገረሱ፤ "እኔ ምንም አልሰማሁም ነው የምልህ። ለምድን ነው የምትጠይቀኝ?" በማለት መልሰዋል።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች የሉም ብለዋል።

ኃላፊው "ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም" ከማለት ውጪ ማብራሪያ መስጠት አልፈለጉም።

አማራ

የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገርም፤ "አሁን ማውራት የማልችልበት ቦታ ነው ያለሁት" በማለት የእጅ ስልካቸውን ዘግተውታል። አቶ አገኘው ተሻገርን መልሰን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከአምስት ቀናት በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ "አራት ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ መረጃው አለኝ" ማለታቸው ይታወሳል።

ታግተው የሚገኙት ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በስልክ አልፎ አልፎ እንደሚገናኙ ጭምር ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ተማሪዎቹ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ከአባ ገዳዎች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት እያደረግን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረትም ስልካቸው ዝግ በመሆኑ አልተሳካም።

Presentational grey line

ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የወሰደው እርምጃ የለም በማለት በርካቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

ከእነዚህ መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ትናንት ባወጣው መግለጫ የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ እና ጥቃት አድራሾቹ ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዛሬ በገፁ ላይ ባወጣው መግለጫም፤ የታገቱት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲለቀቁ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባስቸኳይ እንዲወጣ ጠይቋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

'የታገቱት ተማሪዎች ይለቀቁ' የሚል ዘመቻም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተካሄዱ ነው፤ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥም እየተጠየቀ ነው።

የጠቅላይ ሚንስትሩን ካቢኔዎች 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን በማስታወስ፤ በደህንነት ስጋት የዩኒቨርሲቲ ግቢ ለቀው ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ የታገቱ ሴት ተማሪዎች ትኩረት አለማግኘት በመጥቀስ ብስጭት አዘል አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።