በኬንያ በአውቶብስ ላይ በተፈፀመ ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

በኬንያ በሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በአውቶብስ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በጥቃቱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

አውቶብሱ ከሞምባሳ ተነስቶ እየተጓዘ ሳለ ነበር በላሙ ግዛት የታጠቁ ሰዎች አውቶብሱ እንዲቆም በማስገደድ የጥይት ውርጅብኝ ያዘነቡበት።

የታጣቂዎቹ ማንነት አልታወቀም።

መሠረቱን በሶማሊያ ያደረገው የአል ሻባብ ታጣቂ ቡድን በአገሪቷ በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሰንዝሯል።

ይህንም ጥቃት የሰነዘረው አል-ሸባብ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል።

የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው የተሰወሩትን ጥቃት አድራሾች በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተከታታሉ መሆናቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኬንያ አል ሻባብን ለመዋጋት በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈውን መንግሥት ለመደገፍ በሶማሊያ ወታደሮች አሏት።

የደህንነት መሥሪያ ቤት ያሳለፍነውን ገና እና አዲስ ዓመት በዓል ወቅት አል ሻባብ ጥቃት ሊፈፅም ይችላል ሲል ያወጣውን ሪፖርት ተከትሎ በተጠንቀቅ ቆይታለች።