በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሶስቱ ፓርቲዎች ጥምረት ለብልጽግና ስጋት?

በአገራችን ሕጋዊ እውቅና ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ብዛት ከ100 በላይ የመሆናቸው ዜና ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። የኦሮሞን ህዝብ እና ጥቅም እናስከብራለን ብለው በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ቁጥርም ቢሆን ቀላል የሚባል አይደለም።
ቁጥራቸው ይህን ያህል ይብዛ እንጂ፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችና የህዝብ ድጋፍ ካላቸው ጥቂት ፓርቲዎች መካከል፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እንዲሁም የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ) ተጠቃሽ ናቸው።
እኚህ በክልሉ ተጽእኖ ፈጣሪ ናቸው የሚባሉት ፓርቲዎች፤ ጥምረት ሊፈጽሙ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ኦፌኮን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መቀላቀላቸው የተሰማው አቶ ጀዋር መሐመድ፣ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የሶስቱ ፓርቲዎች ጥምረት በቅርቡ እውን ሊሆን እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል።
አክለውም የሶስቱ ፓርቲዎች ጥምረት ነገ (ዓርብ) ይፋ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ይህ ፓርቲ በፕ/ር መረራ ጉዲና ሊቀ መንበርነት የሚመራ ሲሆን፤ እንደ በቀለ ገርባ እና ጃዋር መሐመድን የመሳሰሉ በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦችን በአባልነት ይዟል።
ኦፌኮ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 'ትልቁ' ፓርቲ ስለመሆኑ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።
ኦፌኮ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሃገራዊ ምርጫዎች ላይም ተሳትፎ ነበር።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
ኦነግ ከተመሰረት ከ40 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል። ከዚህ ቀደም 'ሽብርተኛ' ተብሎ ተፈርጆ የነበረው ኦነግ፤ በርካታ ዓመታትን በትጥቅ ትግል፣ ማሳለፉ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ዳውድ ኢብሳ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ይታወሳል።
ኦነግ ልክ እንደ ኦፌኮ ሁሉ ተጽእኖ ፈጣሪ ስለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙ ሲሆን፣ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜም ተሳታፊ ይሆናል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ (ኦብፓ)
ኦብፓ በብርጋዴር ጀነራል ከማል ገልቹ የሚመራ ፓርቲ ነው። ብ/ጀ ከማል ገልቹ ከፓርቲያቸው አባላት ጋር በኤርትራ እንዲሁም በኡጋንዳ መሽገው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥሪ ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ይታወሳል።
ብ/ጀ ከማል ወደ ሃገር ከተመለሱ በኋላ ለስድስት ወራት ያክል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮን መምራታቸው ይታወሳል።
አብፓ የብ/ጀ ከማል ገልቹ የትውልድ ስፍራ በሆነው አርሲ እንዲሁም በአንዳንድ የባሌ አካባቢዎች ድጋፍ እንዳለው ይታመናል።

ለመሆኑ ሶስቱ ፓርቲዎች ቢጣመሩ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ብልጽግና ፓርቲ የሚፈጥረው አንድምታ ምንድነው?
የኦሮሚያን ፖለቲካ በቅርብ የምትከታተለው የአዲስ ስታንዳርድ መስራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ የሆነችው ጸዳለ ለማ በዚህ ላይ ለቢቢሲ አስተያየቷን ሰጥታለች።
ጥያቄ፡ እነዚህ በክልሉ ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ሶስቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት ቢወስኑ የሚኖረው አንድምታ ምንድነው?
ጋዜጠኛ ጸዳለ፡ ባለኝ መረጃ መሠረት በፓርቲዎቾ መካከል ሶስት አይነት ድርድሮች እየተካሄዱ ነው። አንደኛው ከምርጫው በፊት ሊኖራቸው ስለሚችለው ትብብር፣ ሁለተኛው ከምርጫው በኋላ እንዴት ሊሰሩ እንደሚችሉና ሶስተኛው ደግሞ አንድ ላይ ሆነው ከሌሎች 'የፌደራሊስት ብሎክ' ጋር እንዴት ሊተባበሩ እንደሚችሉ በሚመለከት ንግግር ላይ ናቸው።
በጣም አስፈላጊ የሚመስለኝ ከምርጫ በፊት የሚኖራቸው ንግግር ነው። ሶስቱም ፓርቲዎች ሃገራዊ ፓርቲዎች ስለሆኑ እጩዎቻቸውን በሁሉም አካባቢ የማቅረብ መብት አላቸው። ይህ ማለት ሶስቱም በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ ሊወዳደሩ ይችላሉ። ይህ ግን የመራጩን ድምጽ ይበታትነዋል የሚል ስጋት አለ። ያንን ለማስወገድ ነው ንግግሩ እየተደረገ ያለው።
ሁሉም የየራሳቸው ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች አሏቸው። ለምሳሌ የከማል ገልቹ (ብ/ጀ) በአርሲ አካባቢ ጠንካራ ድጋፍ አለው። ኦነግ ደግሞ በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ ቦረና እና ጉጂ ጠንካራ ድጋፍ አለው። ኦፌኮ ደግሞ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ጥሩ እንቀስቃሴ አለው።
ስለዚህ የመራጮችን ድምጽ ሳይበታተን ፓርቲዎቹ ድጋፍ ባላቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርገው እንዲወዳደሩ እድል ይሰጣል። ከዚህ በተጨማሪም ከምርጫ በፊትና ከምርጫ በኋላ በደጋፊዎቻቸው መካከል ግጭት እንዳይከሰትም የሚያደርግ ንግግር ነው ሶስቱ ፓርቲዎች እያደረጉ ያሉት።
ይህ የሚሳካለቸው ከሆነ አንድምታው ትልቅ ነው። የመጀመሪያው የዲሞክራሲያዊ ምርጫ አንዱ መገለጫ ሰላም ስለሆነ፤ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
ሶስቱ ፓርቲዎች የምርጫ ቀጠናዎችን እየለዩ 'እዚህ አከባቢ ያለኝ ድጋፍ ከዚህ ይበልጣል' በመባባል እርስ በእርስ ከመወዳደር ይልቅ አንዱ ከአንዱ የሚተባበር ከሆነ ይህ ትልቅ ነገር ነው።
ከምርጫ በኋላ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በጨፌ [የኦሮሚኣ ክልል ምክር ቤት] ውስጥ ምን አይነት ጥምረት መፍጠር ይቻላል የሚል ንግግርም እየተካሄደ ነው። እነዚህ ከምርጫ በፊት እና በኋላ የሚደረጉ ውይይቶች ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።
ጥያቄ፡ የእነዚህ ሶስት ፓርቲዎች ጥምረት መፍጠር የተሻለ ድምጽ ሊያስገኝላቸው ይችላል?
ጋዜጠኛ ጸዳለ፡ ያለ ምንም ጥርጥር። ሁሉም በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ ሲወዳደሩ፤ የመራጩ ድምጽ ይበታተናል። ማንም አሸናፊ ሳይሆን ሊቀር ይችላል። ጥምረቱ እውን የሚሆነ ከሆነ፤ ለፓርቲዎችም ሆነ ለድምጽ ሰጪ አዎንታዊ ነገር እንደሆነ ነው የምገነዘበው።
ጥያቄ፡ የሶስቱ ፓርቲዎች ጥምረት ለብልጽግና ፓርቲ አስጊ አይሆንበትም ታዲያ?
ጋዜጠኛ ጸዳለ፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ግለት ለብልጽግና ፓርቲ ይህ አሉታዊ አጋጣሚ ነው። ነገር ግን አንድ መገንዘብ ያለብን ምንም እንኳ የፓርቲዎቹ ጥምረት፤ የብልጽግና ፓርቲን ድምጽ የማግኘት እድልን ቢያጠበውም፤ የገዢው ፓርቲ መዋቅር በጣም ጥልቅ ነው። ስለዚህ ኦዲፒ (ብልጽግና ፓርቲ) ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ይቀጥላል የሚል ዕምነት ነው ያለኝ። የፓርቲዎቹ ጥምረት ኦዲፒ ድምጽ እንዲያጣ ያደርገዋል። ያ ማለት ግን ኦዲፒ ወሳኝነትን ያጣል ማለት አይደለም።
ለኦዲፒ መልካም አጋጣሚው ነበር የመንግሥት መሰረተ ልማት በእጃቸው ነው። ስለዚህ በፈለጉት ጊዜ ይህን ሃብት ለጥቅማቸው ተግባር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ።
ጥያቄ፡ ከምርጫው በኋላ ፓርቲዎቹ የምርጫውን ውጤት ለመቀበል ዝግጅቱ ያላቸው ይመስልሻል?
ጋዜጠኛ ጸዳለ፡ ከምርጫ በፊት የሚያደረጉት ድርድር ፓርቲዎች አቅማቸውን እንዲያወቁት ትልቅ ጥቅም አለው። አንዳንድ ፓርቲዎች የቀደመ ስማቸውን ይዘው ነው እየተወዳደሩ ያሉት። አሁን ለምሳሌ ኦነግ ፖሊስ የለንም ሲሉ ሰምቻለሁ። የቀደመ ዝናቸውን ይዘው ነው እየተወዳደሩ ያሉት።
ፓርቲዎች አንድ አካባቢ ላይ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ እርግጠኛ ሆነው መግባት የለባቸውም። ሽንፈት ሊገጥማቸው እንደሚችል አምነው ነው መቀላቀል ያለባቸው። የሚያደርጉት ንግግር ይህንን ማካተት ይኖርበታል።
ሌላው ሁሉም አካል የምርጫ ውጤትን እንዲቀበል፤ በምርጫ ቦርድ ላይ እምነት ሊኖረው ይገባል። በአሁኑ ሰዓት በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በምርጫ ቦርድ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። አሁን ላይ እኚህ ቅሬታዎች ትንሸና ከባድ ላይመስሉ ይችላሉ። በኋላ ግን መዘዛቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።
ምርጫ ቦርድም፤ ለእነዚህ ቅሬታዎች ምላሽ እየሰጠ የእርስ በእርስ መተማመን ላይ መደረስ ይኖርበታል።
ምርጫው ሰላማዊ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊም መሆን ይኖርበታል። ምርጫው ፍትሃዊ እንዲሆን ሃላፊነቱ የምርጫ ቦርድ ሲሆን፤ ሰላማዊ እንዲሆን ደግሞ ፓርቲዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ከምርጫ በኋላ ሊከሰት የሚችል ግጭትን መቆጣጠር የሚችል ተቋማዊ አቅም የለንም። ፓርቲዎቹ ከምርጫ በኋላ በሚከሰቱ ግጭቶች ማንም እንደማያተርፍ አውቀው አለመግባባት እንዳይከሰት መስረት አለባቸው።
ጥያቄ፡ እኚህ ሶስቱ ፓርቲዎች የሚለዩበት ነገር ምንድነው?
ጋዜጠኛ ጸዳለ፡ በሶስቱ ፓርቲዎች መካከል የሰፋ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት የለም። ልዩነታቸው ድጋፍ ያላቸው በተለያዩ የምርጫ ቀጠናዎች መሆኑ ነው። ኦነግ የተወለደበት ወለጋ አካባቢ ድጋፍ አለው። ዝና አለው።
የመረራ (ዶ/ር) ፓርቲም ቢሆን፤ እርሳቸው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ነው ድጋፍ ያለው።
የከማል ገልቹ (ብ/ጀ) ፓርቲ በተመለከተ አንድ መነሳት ያለበት ቁም ነገር አለ። ይህም የኃይማኖት ጉዳይ ነው። የከማል ገልቹ ድጋፍ በስፋት ያለው አርሲ እና ባሌ ነው ስንል የኦሮሞ ሙስሊም ምርጫ ቀጠናዎች አርሲ እና ባሌ በስፋት መኖሩን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል። የኦሮሞ ሙስሊሞች ምስራቅ ሃረርጌም፣ ድሬዳዋም አሉ። ይሁን እንጂ የኦሮሞ ሙስሊም በስፋት በአንድ ቦታ ተሰባስቦ የሚገኘው በአርሲ እና ባሌ ነው።
ፓርቲዎቹ ልዩነታቸው ምንድነው ብሎ መፈለጉ የሚያለፋ ይመስለኛል።
ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸው ፖሊሲዎች ላይ ተመስርቶ ድመጽ መስጠት የተለመደ ቢሆንም፣ እኛ ሃገር ያለው ባህል ግን ከፖሊሲ ይልቅ በግለሰቦች ላይ ተመስርቶ ነው ድምጽ የሚሰጠው።
ኦፌኮ አዲሱን ቢሯችንን ስናስመርቅ የፓርቲ ፖሊሲያችንን ይፋ እናደርጋለን ብለዋል። ኦነግ ከዚህ በፊት ቃለ መጠይቅ ስናደርግላቸው ቀድሞ የነበራቸው 'የሶሻል ዲሞክራት' አካሄዳቸውን ይዘው ወደ ምርጫ እንደሚገቡ ተገንዝበናል።
ፓርቲዎች ልለዝቡ ምን ይዘው እንደመጡ መጠየቅ አለባቸው። ሆኖም ግን ከፊታችን ባለው ምርጫ ላይ ህዝቡ ድምጹን የሚሰጠው ፖሊሲዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሳይሆን የሰዎች ማንነት ላይ በመመርኮዝ ነው። ሰው ሰውን ነው የሚመርጠው።
















