ጎርፍ በቀላቀለ ወጀብ ተወስደው የነበሩት ላሞች ውቅያኖስ ዳር በሕይወት ተገኙ

ሰሜን ካሊፎርኒያ ውስጥ ሃሪኬን ዶሪያን የተሰኘው ጎርፍ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ባደረሰው ጥፋት ሞተዋል የተባሉ ላሞች ውቅያኖስ ዳር ሲንጎማለሉ ታይተዋል።

ቼዳር ደሴት ላይ ነዋሪ የነበሩት እኒህ ላሞች የተረፉት ውቅያኖስ ላይ ሲዋኙ ከከረሙ በኋላ ሳይሆን አልቀረም ተብሏል።

ሳይሞቱ አልቀረም ተብለው የተገመቱት ላሞች አንድ ውቅያኖስ ዳርቻ ካለ ፓርክ ውስጥ ሳር ሲግጡ ተገኝተዋል።

ሦስቱ ላሞች 8 ኪሎ ሜትር ያህል የውቅያኖስ አካል በዋና ሳያካልሉ አልቀረም የሚሉት የፓርኩ ሰዎች ላሞቹን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ ዕቅድ እየነደፉ ነው።

አንድ የፓርኩ ሠራተኛ ነው ከላሞቹ አንዷ ፓርኩ ውስጥ ስትንጎማለል ባለፈው ወር ያያት። ላሚቱ ከተገኘች ቀናት በኋላ ደግሞ ወዳጆቿ ሣር ሲከረክሙ ተገኝተዋል።

የፓርኩ ባለሙያ የሆኑት ሆርቫርት ላሞቹ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ጥልቅ ሥፍራ አለመጋባታቸው ዕድለኛ ናቸው ይላሉ።

ባለፈው መስከረም ሃሪኬን ዶሪያን ጎርፍ የቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ሲጥል በጎርፍ የተወሰዱ በርካታ ፈረሦች ነበሩ ተብሏል።

የፓርኩ ባለሙያ ላሞቹ በ8 ኪሎ ሜትር ዋናቸው ስንቱን እንዳሳለፉ በመገመት «መቼም ብዙ የሚካፍሉን ታሪክ ይኖራል» ሲሉ ቀልድ ጣል አድርገዋል።

ሃሪኬን ዶሪያን መስከረም ላይ ወጀቡን ሰሜን ካሊፎርኒያ ላይ ሲያሳርፍ ንብረት እና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

ይህ ወጀብ ወደ ባሃማስ ደሴት አቅንቶ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እንዳደረሰ አይዘነጋም።