ካዱና ትምህርት ቤት፡ "ማሰቃያ ቤቱ እንደ ሲኦል ነው"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በናይጀሪያ አንድ ማሰቃያ ቤት ታጉረው የነበሩ በርካታ ሰዎች ፖሊስ ባደረገው ክትትል ነፃ መውጣታቸው ይታወሳል። ከእነዚህ ፖሊስ ከታደጋቸው ግለሰቦች አንዱ የሆነው ኢሳ ኢብራሂም ሁኔታው በገሃነመ እሳት ውስጥ እንደመኖር ነው ሲል ይገልፀዋል።
"ስትፀልይም፤ ስታነብም ይበድቡሃል" ሲል የ29 ዓመቱ ኢሳ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሕፃናትን ጨምሮ ቁጥራቸው 500 የሚሆኑ ወንዶች በናይጀሪያ ካዱና በሚገኝ እና ለእስልምና ትምህርት ቤት ያገለግል ከነበረ ሕንፃ በፖሊስ እርዳታ ነፃ ወጥተዋል።
ፖሊስ እንዳስታወቀው ቦታው ሰዎች በባርነት የተሰቃዩበትና አብዛኞቹ በእግረ ሙቅ ታስረው ነበር የተገኙት።
አንዳንዶቹ ተጠቂዎች የተሰቃዩ ሲሆን የወሲብ ጥቃትም የደረሰባቸው መኖራቸውን የአገሪቷ ባለሥልጣን አስታውቋል።
የማጎሪያ ህንፃውን የጎበኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ኢሳቅ ካሊድ እንዳለው ተመሳሳይ ድርጊቶች የሚፈፀሙባቸው ሌሎች ተቋማት ሊኖሩ እንደሚችል ጥርጣሬ አላቸው።
በናይጀሪያ አብዛኛው ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ትምርት ቤት ለመላክ አቅማቸው ስለማይፈቅድ በቂ ክትትልና ቁጥጥር የማይደረግባቸው ወደ እንደዚህ ዓይነት ተቋማት ይልካሉ።
በዚህ ተቋም ፊት ለፊት 'አህመድ ቢን ሃምበል የእስልምና ትምህርት ማዕከል' የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሎ የሚታይ ሲሆን መጥፎ ሥነ ምግባር ያላቸውን ወጣት ወንዶች በባህሪ ለማረቅ ይጠቀሙበትም እንደነበር ተመልክቷል።
የካዱና ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ኩቡ ሳቦ "ይህ የሰብዓዊ ጥሰት የተፈፀመበትን ቦታ የእስልምና ትምህርት ቤት ነው ለማለት ያስቸግራል" ብለዋል።
ቦታው ከወላጆች ክፍያ ሲቀበል የነበረ ቢሆንም እንደ ትምህርት ቤትም ሆነ እንደ የባህሪ ማረሚያ ተቋም የተመዘገበ አለመሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የተወሰኑ የተቋሙን ሠራተኞች ጨምሮ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈፀምባቸው ተቋማት ካሉ ለማጣራት ተጨማሪ ምርመራ እያደረኩ ነው ሲል መንግሥት አስታውቋል።
በተለይ በሰሜን ናይጀሪያ ክፍል የፀባይ ማረሚያ ትምህርት ቤቶች ጥቃት እንደሚፈፀም የተለያዩ መረጃዎች ይወጣሉ። አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎቹ በትርፍ ጊዜያቸው በጎዳና ላይ ለልመና እንዲወጡ ይገደዳሉ ብሏል ሪፖርቱ።
ኢሳ ኢብራሂም ባህሪውን ለማረቅ ሲሉ ወላጆቹ ወደ ትምህርት ቤት የላኩት ከሁለት ሳምነንታት በፊት ነበር።
እርሱ እንደሚለው ፖሊሶቹ ከመድረሳቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ለማምለጥ ሞክሮ ነበር።
እግሮቹ በሰንሰለት ታስረው ከአንድ አሮጌ ጀኔሬተር ጋር አቆራኝተውት ስለነበር ማምለት አልቻለም። ኢሳ ጭካኔ የተሞላበት ድብደባም ይፈፀምበት እንደነበር ይገልፃል። ቅጣቱ 'ታርኪላ' ይሰኛል እጃቸው ወደላይ ታስሮ ከጣሪያ ላይ እንዲንጠለጠል በማድረግ ነው የሚፈፀመው።
"በጣም ብዙ ጉዳቶች ደርሰውብኛል፤ ሁሉም የሰውነት ክፍሌ ተጎድቷል፤ ብንተኛ እንኳን ከእንቅልፋችን እየቀሰቀሱ ይደበድቡናል" ይላል።
ኢሳ እንደሚለው ምግብ ይሰጧቸው እንዳልነበርና ከሰጧቸውም ነጭ ሩዝ ብቻ እንደነበር ይናገራል።
በሕንፃው ውስት የነበሩት ሰዎች ምግብ ስለማይሰጣቸው አቅማቸው ተሟጦ አልቆ ነበር።
ከአምስት ዓመት የሚያንሱ ሕፃናት ነፃ ከወጡት የሚገኙበት ሲሆን አብዛኞቹ ከናይጀሪያ ሲሆኑ ሁለቱ ግን ከቡርኪና ፋሶ የመጡ እንደሆኑም ተዘግቧል።
የካዱና ባለሥልጣናት በግዛቷ የሚገኙ ሌሎች የእስልምና ትምህርት ቤቶች ላይ ፍተሻ እንደሚደርጉ አስታውቀዋል።













