አንጎላዊያኑ በደቡብ ኮሪያ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ዘጠኝ ወራትን አስቆጠሩ

አንጎላውያን ስደተኞች በሴዑል አውሮፕላን ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሴዑል አውሮፕላን ማረፊያ

ከአንድ ሃገር ወደ ሌላ ሃገር ለመሄድ ወይም ደግሞ ከአሰቡት ሃገር ከደረሱ በኋላ በቪዛና በመሰል ጉዳዮች ምክንያት አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ መጉላላት ደርሶብዎት ያውቃል? ጊዜውስ ምን ያክል ሊሆን ይችላል? አንድ ቀን? ሳምንት? ወይስ አንድ ወር?

በአንጎላውያን ቤተሰቦች ላይ የደረሰው መጉላላት ግን ምናልባትም የእርሰዎን መጉላላት "ምንም" የሚያስብል ሊሆን ይችላል።አንጎላውያኑ የሉሌንዶ ቤተሰቦች የዘር ሃረጋቸው ከአናሳ ጎሳ የሚመዘዝ ነው።

እነዚህ ቤተሰቦች ታዲያ "በሃገራችን በሰላም እንኖር ዘንድ መንግሥት ያሰማራቸውን ፖሊሶች ግርፋትና ጭቆና ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ሆኖብናል" በማለት የሃገራቸውን መንግሥት ምድራዊ በዳያቸው በማድረግ ያወግዛሉ።

በደሉን ባለማቆሙም ጭቆናና ግርፋቱን ለማምለጥ ቤተሰቦቹ ባለፈው አመት በወርሃ ታህሳስ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሩቅ ምስራቅ ደቡብ ኮሪያ አምርተዋል።

በደቡብ ኮሪያም የተንደላቀቀና ነጻነት የተሞላበት ህይወት እንደሚኖራቸው ጥርጥር አልነበራቸውም።

ደቡብ ኮሪያ ሴዑል አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ በኋላ የገጠማቸው ነገር ግን ያልጠበቁት ነበር።

እድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ አራት ህጻናትን ጨምሮ አጠቃላይ የሉሌንዶ ቤተሰቦች ደቡብ ኮሪያ የመኖር መብት እንደሌላቸውና ጉዟቸውም ከንቱ ልፋት እንደሆነ ተነገራቸው።

ለስደት የዳረጋቸውን ዝርዝር ምክንያት ለደቡብ ኮሪያ የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ ቢያስረዱም "ምክንያታችሁ አላሰመነኝም" በማለት የመኖሪያ ፍቃድ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎባቸዋል።

"ወደሃገራችን ከመመለስ ምንም መሆን የተሻለ ነው" ብለው ያመኑት የሉሌንዶ ቤተሰቦች ግን የተሰጣቸው ተስፋ አስቆራጭ ምላሽ ከዛሬ ነገ በበጎ ምላሽ ሊቀየር ይችላል በማለት የደቡብ ኮሪያ ሴዑል አየር ማረፊያን ቤታቸው አድርገው መኖር ከጀመሩ እነሆ ዘጠኝ ወራትን አስቆጠሩ።

በአሁኑ ወቅት የቤተሰቦቹ "ደቡብ ኮሪያ እንኑር ማመልከቻ" የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት ጋር ደርሶ ጉዳያቸው እንዲመረመር የስደተኞች ጉዳይ ቢሮ በሃገሪቱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ነገር ግን ከአሁን በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ ስደተኞች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት ማመልከቻቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል።

ከዚህ አንጻር ዘጠኝ ወር የጠበቁት የሉሌንዶ ቤተሰቦች ዕጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን ይችላል?

የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው ቢባልም አመልካቾቹ ግን አሁንም የደቡብ ኮሪያን በጎ ምላሽ እየሻቱ አስረኛ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ኑሯቸውን ጀምረዋል።

ምናልባትም አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በመኖር "ክብረ ወሰን" የሚሆን ጊዜን እያስመዘገቡም ይሆናል።