አሜሪካ፡ ''ሳዑዲን ያጠቁት ድሮን እና ሚሳዔሎች መነሻቸው ከኢራን ነው''

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ ሳዑዲ ላይ የተቃጡትየድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች መነሻቸው ከኢራን ስለመሆኑ ደርሼበታለው አለች።
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማትን ዒላማ አድርገው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱት ጥቃቶች መነሻቸው ከደቡባዊ ኢራን ነው።
ኢራን በበኩሏ ከጥቃቶቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ስትል ቆይታለች።
በየመን የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን በሳዑዲ ጥቃቱን ያደረስነው እኛ ነን ቢሉም ሰሚ አላገኙም።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢንርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው'' ለማለት ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።
ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ጥቃቱ የተሰነዘረበት አቅጣጫ እና ስፋት ከግምት ውስጥ ሲገባ የሁቲ አማጽያን ፈጽመውታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።
የሁቲ አማጽያን ከዚህ ቀደም ወደ ሳዑዲ የድሮን ጥቃቶችን አድርሰዋል፤ ሚሳዔሎችንም አስወንጭፈዋል። የአሜሪካ ባለስልጣናት ይህን ጥቃት ግን የሁቲ አማጽያን መፈጸም የሚያስችል ቁመና የላቸውም፤ እንዲሁም ጥቃቶቹ የተሰነዘሩት በየመን የሁቲ አማጽያን ከሚቆጣጠሩት ስፍራም አይደለም።
በሳዑዲ ላይ ጥቃቱ ከተሰነዘረ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጨማሪ ማሳየቱ ይታወሳል።
የሳዑዲ አረቢያ ኢነርጂ ሚንስትር ትናንት (ማክሰኞ) በነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማቱ ላይ የደረሰው ጉዳት ተጠግነው ወደ ቀደመ የማምረት አቅማቸው በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ይመለሳሉ ብለዋል።
አሜሪካ ምን እያለች ነው?
የአሜሪካ ባለስልጣናት የሳዑዲን ነዳጅ ማቀነባበሪያ ለመምታት ጥቅም ላይ የዋሉት የድሮን እና ሚሳዔል አይነቶችን ለይተናል ብለዋል።
ጥቃቱ ከደረሰበት ስፍራ በሚሰበሰቡ ቁሶች ላይ የሚደረገው የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ኢራን እጇ እንዳለበት የማያወላውል መረጃ ማሳየታቸው አይቀሬ ነው እያሉ።
ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ ትናንት "አሜሪካ ሁሉንም መረጃዎች እየመረመረች ነው" ካሉ በኋላ የውጪ ጉዳይ ቢሮው ኃላፊ ማይክ ፖምፔዎ "ምላሻችን ምን መሆን አንዳለበት ለመወያየት" ወደ ሳዑዲ እያቀኑ ነው ብለዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የእራሷን እና የወዳጅ ሃገራትን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ከመውሰድ ወደኋላ አትልም። በዚህ እርግጠኛ ሁኑ" ሲሉ ምክትል ፕሬዝደንት ማይክ ፔንስ ተደምጠዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት ፕሬዝደንት ትራምፕ ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ "አቀባብለን" የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው በማለት ወታደራዊ አማራጭ ከግምት ውስጥ እንደገባ አመላክተዋል።
የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጃቫድ ዛሪፍ በትዊተር ገጻቸው ላይ አሜሪካ እውነቱን አምና መቀበል አልፈለገችም ካሉ በኋላ ይህን ሁሉ እስጥ አገባ ማስቆም የሚቻለው በየመን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ማስቆም ሲቻል ነው ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ













