በሳዑዲ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

በሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋም ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋም ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ

በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ የዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪ አሳየ።

ቅዳሜ ዕለት በሁለት የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ቦታዎች ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ለዓለም የሚቀርበው የነዳጅ መጠን አምስት በመቶ ቀንሷል።

በዚህም ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከ15 እስከ 19 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በድሮን ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው የሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪ ተቋማት ወደ ቀደመ ስራቸው ለመመለስ ሳምንታት ያስፈልጋለል ተብሏል።

ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተሰነዘረባቸው የሳዑዲ ነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋማት በዓለማችን እጅግ ዘመናዊ እና ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው የነዳጅ ማቀነባበሪያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ጥቃቱን ማን ሰነዘረው?

በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የድሮን ጥቃቱን የፈጸምነው እኛ ነን ብለዋል።

አሜሪካ ግን ሳዑዲ ላይ ለደረሰው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርጋለች። የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ከምዕራባውያን መንግሥታት ድጋፍ የሚያገኘው ሳዑዲ መራሹ ኃይል በየመን እየተደረገ ባለው ጦርነት ለየመን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ኢራን ደግሞ ለሁቲ አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢንርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው'' ብለዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በበኩላቸው ለጥፋቱ ማን ተጠያቂ እንደሆነ ስለምናውቅ "አቀባብለን" የሳዑዲ መንግሥት ምክረ ሃሰብ ምን እንደሆነ እየጠበቅን ነው ብለዋል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

የሳዑዲ ባለስልጣናት ጥቃቱ በሰው ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም በማለት የድሮን ጥቃቱ ስላደረሰው ጉዳት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ቀርተዋል። የተሰነዘረው ጥቃት የሳዑዲ አረቢያን የድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅም በግማሽ መቀነሱ ግን ተረጋግጧል።

ሳዑዲ አረቢያ የዓለማችን ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች ስትሆን በየቀኑ ወደ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ውጪ ሃገራት ትልካለች።

የሁቲ አማጺያን እነማን ናቸው?

በኢራን መንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የየመንን መንግሥት እና የሳዑዲ መራሹን ኃይል ሲፋለሙ ቆይተዋል።

ፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ከመዲናዋ ሰነዓ በሁቲ አማጽያን ተባረው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የመን ላለፉት 4 ዓመታት በጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።

ሳዑዲ ከመዲናዋ የተባረሩትን ፕሬዝደንት በመደገፍ በሁቲ አማጽያን ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ የአየር ጥቃቶችን ትፈጽማለች። የሁቲ አማጽያን በበኩላቸው ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ ያስወነጭፋሉ።