አሜሪካ ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አደረገች

Fire at Saudi plant at Abqaiq

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮ ቅዳሜ ዕለት የሳዑዲ ነዳጅ ማውጫ ተቋማት ላይ ለተሰነዘረው የድሮን ጥቃት ኢራንን ተጠያቂ አድርገዋል።

የሁቲ አማጺያን ትናንት ሳዑዲ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን እንወስዳለን ቢሉም ማይክ ፖምፔዮ ግን አጣጥለውታል። የሳዑዲ አረቢያ የሃይል ሚንስቴር እንዳስታወቀው የተሰነዘረው ጥቃት የሳዕዲ አረቢያን የድፍድፍ ነዳጅ የማምረት አቅም በግማሽ ቀንሶታል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ሳዑዲ ላይ የተፈጸመው ጥቃት በዓልም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ላይ የዋጋ ልዩነት ሊያስከትል ይችላል።

ከምዕራባውያን መንግሥታት ድጋፍ የሚያገኘው ሳዑዲ መራሹ ኃይል በየመን እየተደረገ ባለው ጦርነት ለየመን መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፤ ኢራን ደግሞ ለሁቲ አማጽያን ድጋፍ ታደርጋለች።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊው ማይክ ፖምፔዮ ''የድሮን ጥቃቱ ከየመን ስለመነሳቱ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ የለም። ሁሉም መንግሥታት ኢራን በዓለም የኢንርጂ ምንጭ ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ማውገዝ አለበት'' ብለዋል።

የሁቲ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ከ10 በላይ የድሮን ጥቃቶች መሰንዘራቸውን እና ወደፊትም ተመሳሳይ ጥቃቶች ሳዑዲ ላይ እንደሚሰነዘሩ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ መቀመጫውን ቤሩት ላደረገው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ "ይህ ትልቅ ኦፕሬሽን ማሳከት የቻልነው በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ የተከበሩ ሰዎች ድጋፍ ጭምር ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

ጥቃቱ ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ ከሳዑዲ መንግሥት ባለስልጣናት የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም፤ የሳዑዲ አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር "ሳዑዲ ለዚህ መሰል የሽብር ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን" ነግረዋቸዋል።

ዋይት ሃውስ ሳዑዲ እራሷን መከላከል እንድትችል አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆኗ ትራምፕ ለሳዑዲ ባለስልጣናት አስታውዋል።

የሁቲ አማጺያን እነማን ናቸው?

በኢራን መንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው የሁቲ አማጽያን የየመንን መንግሥት እና የሳዑዲ መራሹን ኃይል ሲፋለሙ ቆይተዋል።

ፕሬዝደንት አብደራቡህ ማንሱር ከመዲናዋ ሰነዓ በሁቲ አማጽያን ተባረው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ የመን ላለፉት 4 ዓመታት በጦርነት ስትታመስ ቆይታለች።

ሳዑዲ ከመዲናዋ የተባረሩትን ፕሬዝደንት በመደገፍ በሁቲ አማጽያን ላይ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ የአየር ጥቃቶችን ትፈጽማለች። የሁቲ አማጽያን በበኩላቸው ሚሳኤሎችን ወደ ሳዑዲ ያስወነጭፋሉ።