የየመን ጦርነት፡ የሁቲ አማፂያን የሁዴይዳን ወደብ ለቀው እየወጡ ነው

የሁቱ አማፂያን በሁዴይዳ ወደብ በመኪና ላይ ሆነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ባለፈው ታህሳስ ወር ከተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ የየመን ሁቲ አማፂያን ቁልፍ የሆኑ ወደቦችን ለቀው መውጣት ጀምረዋል። ይህም ከስምምነቱ በኋላ በየመን ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መልኩ ለመቋጨት ዋና እርምጃ እንደሆነ ተነግሯል።

የሁቲ አማፂያንና የመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ከሁዴይዳ ወደብ ለቀው የወጡት በአካባቢው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ለማስቻል ነው ተብሏል።

ይሁን እንጂ የየመን መንግሥት አማፂያኑ ሁኔታውን ለመቀልበስ የተጠቀሙት ዘዴ ነው ሲል እምነት እንዳልጣሉባቸው ገልጿል።

የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረው አል ሃሰን ታሄር አማፂያኑ በሌሎች የሁቲ ወታደሮችን ተክተዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ቢቢሲ ያስቀረው ተንቀሳቃሽ ምስል የሁቱ አማፂያን ከአንድ መኪና ላይ ተሳፍረው ሲወጡ የሚያሳይ ሲሆን ወታደሮቹ በአራት ቀን ውስጥ በሌላ ቦታ ይመደባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል የተባበሩት መንግሥታትን ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅን ጠቅሶ እንደዘገበው አማፂያኑ ለቀው እየወጡ መሆናቸው ተዘግቧል።

በየመን የተባበሩት መንግሥታት መልዕክተኛ እንዳሉት አሁን እየሆነ ያለው የመጀመሪያ እርምጃ ነው ።

"በዚህ እርምጃ የየመን መንግሥት ደስተኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የቤት ሥራ ይጠብቀናል" ሲሉ ማርቲን ግሪፊት ለቢቢሲ ተናግረዋል። በሁለቱም ወገኖች ዘንድ አለመተማመን እንዳለም አክለዋል።

በየመን ባለፉት አራት ዓመታት በነበረው የርስ በርስ ጦርነት በትንሹ 6,800 የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች የተገደሉ ሲሆን ከ10,700 በላይ የሚሆኑት ለጉዳት ተዳርገዋል።

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈው ቀድሞ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ፤ እንደ የተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ በሽታዎች፣ ደካማ የጤና እንክብካቤ መኖር ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።