ከወርቅ የተሰራው የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ተሰረቀ

ከወርቅ የተሰራው የሽንት ቤት መቀመጫ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

እንግሊዝ ውስጥ በ18 ካራት ወርቅ የተሰራ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ከብሌንሄይም ቤተ-መንግሥት መሰረቁ ተሰምቷል።

አንድ የዘራፊዎች ቡድን ወደ ቤተ-መንግሥቱ ሰብሮ በመግባት ይህንን ድንቅ የጥበብ ስራ ሰርቀዋል ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ይህ መጸዳጃ ቤት መቀመጫ (ሲንክ) አሜሪካ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ጎብኚዎች ወደ ቤተ-መንግሥቱ ሲመጡ መጠቀም ይችሉ እንደነበር ተገልጿል።

መቀመጫው እስካሁን የት እንዳለ ባይታወቅም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ግን አንድ የ66 ዓመት ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል። ዘራፊዎቹ የሽንት ቤት መቀመጫውን ነቅለው ሲወስዱ የውሃ ማስተላለፊያው በመፈንዳቱ ክፍሉ በውሃ መሞላቱን ፖሊስ አስታውቋል።

ባለፍነው ሐሙስ በቤተ-መንግሥቱ በተከፈተው የስነ-ጥበብ ኤግዚቢሽን ለህዝብ ቀርቦ የነበረው የወርቅ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ (ሲንክ) የተሰራው በጣልያናዊው አርቲስት ማውሪዚዮ ካቴላን ነበር።

የእንግሊዙ ታዋቂ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ሰር ዊንስተን ቸርችል የተወለዱበትና የ18ኛው ክፍለዘመን ስሪት የሆነው ቤተ-መንግስሥት በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። ነገር ግን ከስርቆቱ በኋላ ምርመራው እስኪጠናቀቅ በማለት ለጎብኚዎች ዝግ እንዲሆን ተደርጓል።

North Steps at Blenheim Palace

የፎቶው ባለመብት, John Lawrence

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት የሚገኙት የፖሊስ መርማሪ ጄስ ሚልን እንደገለጹት ከወርቅ የተሰራውን የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ለመስረቅ ዘራፊዎቹ ቢያንስ ሁለት መኪናዎችን ተጠቅመዋል።

''እስካሁን ንብረቱን ማስመለስ ባንችልም የምርመራ ስራችንን አጠናክረን ቀጥለናል። በቅርቡም ውጤት እንደምናገኝና ተጠያቂዎቹን ህግ ፊት እንደምናቀርብ ተስፋ አደርጋለሁ።'' ብለዋል።

ከወርቅ የተሰራው የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ እ.አ.አ. በ2017 ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስጦታ መልክ እንዲወስዱት ተጠይቀው ነበር።