የ14 ዓመቱ አሜሪካዊ 5 የቤተሰቡን አባላት መግደሉን አመነ

በአሜሪካ አላባማ ግዛት አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ 5 የራሱን ቤተሰብ አባላት መግደሉን እንዳመነ የአሜሪካ ፖሊስ ገልጿል።
ታዳጊው ሁሉንም የገደላቸው በሽጉጥ ሲሆን ሟቾች ወላጅ አባቱ፣ እንጀራ እናቱ እንዲሁም ወንድም እና እህቶቹ መሆናቸው ታውቋል። በጥይት ከመታቸው መካከል ሶሰቱ ወዲያው ሲሞቱ ሁለቱ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው እንዳለፈ ፖሊስ አስታውቋል።
በስም ያልተጠቀሰው ታዳጊ ከፖሊስ ጋር እየተባበረ መሆኑን የአከባቢው ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የ14 ዓመት ታዳጊው የእራሱን የቤተሰብ አባላት ለመግደል ምን እንዳነሳሳው የሚጠቁሙ መላ ምቶች እስካሁን እንደሌሉ እና ግድያውን ፈጸመበት ባለ 9 ሚሊ ሜትር ሽጉጥ ከየት እንዳመጣም እስካሁን አልታወቀም።
ግድያው የተፈጸመው ሰኞ ምሽት በአላባማ ግዛት ሲሆን፤ መርማሪዎች እንደሉት ወንጀሉን የፈጸመው ታዳጊው የተኩስ ድምጽ መስማቱን ለፖሊስ ደውሎ ተናግሮ ነበር። ከዚያም ግድያውን እራሱ መፈጸሙን እንዳመነ የአከባቢው ፖሊስ ኃላፊ ተናግረዋል።
ሟቾቹ የ38 ዓመት ጎልማሳው አባቱ ጆን ሲስክ፣ የ36 ዓመት እንጀራ እናቱ ሜሪሪ ሲስክ እንዲሁም የ5 እና 6 ዓመት እንዲሁም የአንድ ወር እድሜ ያላቸው ወንድም እና እህቶቹ መሆናቸው ታውቋል።
በአሜሪካ ጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም ሰዎችን መግደል የተለመደ ነገር እየሆነ ይመስላል። በዚህ ዓመት ብቻ በአሜሪካ ወደ 300 የሚጠጉ የጅምላ ተኩሶች ተፈጽመዋል።
ከቀናት በፊት በሌላ የጅምላ ተኩስ በቴክሳስ ግዛት 7 ሰዎች ተገድለው ነበር። ከዚያ በፊት ደግሞ በቴክሳስ ትልቋ ከተማ ኤል ፓሶ እና ዳይተን 31 ሰዎች ተገድለዋል።












