ከአርባ የሚበልጡ ስደተኞች በሊቢያ ባህር ዳርቻ ሰመጡ

አውሮፓን ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአርባ የሚበልጡ ስደተኞች በሊቢያ ባህር ዳርቻ እንደሰመጡ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተራድዖ ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) አስታውቋል። ስደተኞቹን አሳፍራ የነበረችው ጀልባ መስመጧንና ስልሳ የሚሆኑትን ማዳን እንደተቻለም የየኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ ቻርሊ ያክስሌይ ገልፀዋል።

ስደተኞቹንም ከትሪፖሊ 100 ኪ.ሜትር ርቀት በምትገኘው የባህር ዳርቻ ከተማ አል ኮምስ መጥተዋል።

የሃገሪቷ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ከአካባቢው አሳ አጥማጆች ጋር በመተባበር ግለሰቦቹን በማትረፍ ሂደቱ በመረባረብ ላይ እንደቀጠሉም ዩኤንኤችሲአር በድረገፁ አስታውቋል።

"አይቀሬ አደጋዎች ናቸው የሚለው አስተሳሰብ ማስወገድ አለብን፤ በባህር ህይወታቸውን እየቀጠፉ ያሉትን ማዳን ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያውም ህይወታቸውን እንዲህ አደጋ ላይ ጥለው የሚያሰድዳቸው ጉዳይ ምንድን ነው የሚለውን መፍትሔ ልናበጅለት ይገባል" በማለት በማዕከላዊ ሜድትራንያን የዩኤንኤችሲአር ልዩ መልዕክተኛ ተናግረዋል።

የዩኤንኤችሲአር ቡድንም ከአደጋው ለተረፉት የህክምናና ሰብአዊ እርዳታዎችን በመለገስ ላይ ናቸው።

በያዝነው አመትም በሜድትራንያን ባህር ስደተኞችን አሳፍራ የነበረች ጀልባ ሰምጣ አሰቃቂ የሚባል አደጋ ደርሶ 150 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

አሁን የደረሰውን አደጋ ጨምሮ ከጥር ወር ጀምሮ ባለው አውሮፓ ለመድረስ በሚል ተስፋ የሜድትራንያን ባህር ሲያቋርጡ 900 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የበርካታ ሰዎችን ህይወት መቀጠፍ ተከትሎም ዩኤንኤችሲአር የተባበረ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አፅንኦት በመስጠት ለአውሮፓ ህብረት ሃገራትም ነፍስ አድን መርከቦች እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በባህርም ላይ ሆነ በአየር የነፍስ አድን የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ህጋዊም ገደብ ሊነሳ ይገባል ብሏል ድርጅቱ።

በወደብ አካባቢ የሚገኙ ሃገራት በፍቃደኝነት ላይ የሚስሩ የነፍስ አድን ሰራተኞችን ማበረታታት እንጂ መከልከል እንደማይገባ ድርጅቱ ድረገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ስደተኞችን ከሊቢያ አውጥቶም ወደተሻለ ስፍራ በመውሰድ የተደላደለ ህይወት እንዲኖሩ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል።

የዩኤንኤችሲአር ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሌመንትስ ከሰሞኑ በሊቢያ የሚገኘውን ሰብአዊ ቀውስ ተገኝተው የተከታተሉ ሲሆን በእስር ላይ ያሉ ስደተኞችም ሊለቀቁ ይገባል ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሯ አክለውም 4800 የሚሆኑ ስደተኞችን ለማስለቅ ከሊቢያ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።