የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባልተጠሩበት የቡድን 7 ስብሰባ ላይ ድንገት ተገኝተዋል

የኢራን አርማ ያለበት አውሮፕላን የቡድን 7 ስብሰባ እየተከናወነ ያለበት ቦታ መታየቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ነበር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የኢራን አርማ ያለበት አውሮፕላን የቡድን 7 ስብሰባ እየተከናወነ ያለበት ቦታ መታየቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ነበር

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለሥልጣን በቡድን 7 ሃገራት ስብሰባ ላይ ድንገት በመገኘት ብዙዎችን አጀብ አሰኝተዋል።

ሞሐመድ ያቫድ ዛሪፍ ፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 7 ውይይት ላይ ድንገት መገኘታቸውን የሚያሳብቅ አንድ ፎቶ ማሕበራዊ ድር አምባ ላይ ለቀዋል።

የሰባቱ ሃገራት መሪዎች ከሚያከናውነት ስብሰባ ጎን ለጎን የሚከናወኑ አነስተኛ ውይይቶች ላይ የተሳተፉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብዙዎችን ማስደነቃቸውን ምንጮች ዘግበዋል።

በተለይ የአሜሪካ ልዑካን በከፍተኛ ባለሥልጣኑ 'ድንኳን ሰበራ' እጅግ መደነቃቸውን ከፈረንሳይ የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ።

ሚኒስትር ዛሪፍ በትዊተር ገፃቸው ላይ 'ከፈረንሳይ ፕሬዝደንት እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ገንቢ የሆነ ውይይት አካሂደናል' ሲሉ ፅፈዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቡድን 7 ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ከኢማኑዔል ማኽሮን ጋር መምከራቸው አይዘነጋም።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, JAVAD ZARIF

አሜሪካ እና ኢራን አሁን ላይ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚገኙ መሆኑ የሰውየውን ድንገተኛ ጉብኝት 'ነገሩ ወዴት እና እንዴት ነው?' አድርጎታል።

ፈረንሳይ፤ ኢራን ከአሜሪካ እና ሌሎች አውሮጳ ሃገራት ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙት ለማለሳለስ ብትታርም ኢራን 'የበላችበትን ሳህን ሰባሪ' እየሆነች አስቸግራለች። በተለይ በቅርቡ ከነዳጅ ተሸካሚ መርከቦች ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ክስተት ኢራንን 'ነገር ተንኳሽ' አስብሏታል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሚኒስትር ዛሪፍ ከአሜሪካ ጋር ተስማምተን ነው እንዲጎበኙን ያደረግነው ቢሉም የዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ግን በጉብኝቱ እጅግ መደነቃቸውን አልደበቁም።

የቡድን 7 ሃገራት - ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ስቴትስ፤ ቅዳሜ እና አሁድ 45ኛ ስብሰባቸውን አከናውነዋል።