ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባለቤታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ያልጠበቁት የገጠማቸው አሜሪካዊ አዛውንት
ከሳምንት በፊት ኤል ፓሶ ቴክሳስ ውስጥ በተፈጸመ የጅምላ ግድያ ሚስታቸውን ያጡት አዛውንት በሚስታቸው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ባልጠበቁት ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመገኘታቸው ደንግጠው ነበር።
አዛውንቱ አንቶንዮ ባስኮ ዘመድ አዝማድ ስላልነበራቸው ለባለቤታቸው ቀብር ላይ በዙሪያቸው የሚኖሩ ሰዎችን ብቻ ነበር በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ የጠሩት።
አንቶንዮ ጥቂት ሰዎች በባዶው የቤተክርስቲያን አዳራሽ ወስጥ በመገኘት የሃዘናቸው ተካፋይ በመሆን ለባለቤታቸው የመጨረሻ ስንብት ያደርጋሉ ብለው ነበር የጠበቁት።
ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አዳራሹ ለመግባት ተሰልፈው ሲመለከቱ በጣም ነበር የደነገጡት።
ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተገኘው ሕዝብ ቁጥር አዳራሹ ከሚችለው በላይ ስለነበረ ቀብሩን የሚያስፈጽመው ድርጅት ስንብቱ ሰፋ ባለ አዳራሽ እንዲካሄድ አድርጓል።
ሚስታቸውን በታጣቂ ጥይት የተነጠቁት ሃዘንተኛው አዛውንትም ሊያጽናኗቸው በተሰበሰቡት ሰዎች ብዛት ተደንቀው "የማይታመን ነው!" በማለት ነበር መደነቃቸውን የገለጹት።
አንድ ታጣቂ በገበያ አዳራሽ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ከተገደሉት 22 ሰዎች መካከል አንዷ ለሆኑት የ63 ዓመቷ ባልቴት የአንቶኒዮ ባለቤት ማጊ ሬካርድ የመጨረሻ ስንብት የተሰበሰበው ሰው 700 እንደሚደርስ ተነግሯል።
ሰልፉም ረጅም የነበረ ሲሆን ለአዛውንቱ ሃዘናቸውን ለመግለጽ በርካታ ሰዎች ከተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች መጥተው ነበር።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከ900 በላይ የአበባ ጉንጉኖች ከእስያ አህጉር ጭምር ለስንብት ሥነ ሥርዓቱ ተልኳል።