ባልተጨበጡ የሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳቦች ያምናሉ?

በሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳብ [ኮንስፓይሬሲ ቲዮሪ] ያምኑ ይሆን? መልስዎ አዎ ከሆነ የምንኖርባት ዓለም አሁን ከምናውቀው እጅግ የራቀ መልክ ነው የሚኖራት።

የእንግሊዝ ነገሥታት ከሌላ ዓለም የመጡ ተሳቢ እንስሳት ናቸው፣ ተዋናይ ሮበርት ዴ-ኒሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ማላላ ዮሱፋዛይን ለማስገደል አሢሯል፣ የናይጄሪያው ፕሬዝደንት አስመሳይ ሱዳናዊ ናቸው፣ ኤድስ እና ኢቦላ በሲአይኤ ነው የተፈበረኩት እና ምድር ጠፍጣፋ ነች።

እነዚህ እንግዲህ እስከዛሬ ከተነገሩ የሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳቦች እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው [እኔና እርስዎም አምነንባቸው ሊሆን ይችላል]።

የሤራ ትንተና ፅን-ሐሳብ እውን ላይሆን ይችላል፤ የሚያደርሰው አደጋ ግን በዓይን የሚታይ ነው። ምሳሌ እንድናስቀምጥ ይፍቀዱልን።

ክትባት ገዳይ እንጅ ፈዋሽ አይደለም ብለው በሚያምኑ ሰዎች ወሬ ምክንያት በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ፣ ፈረንሳይ እና ማዳጋስካር [ከብዙ በጥቂቱ] የኩፍኝ ወረርሽኝ ማንሠራራቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

እና እውነታውን ከሤራ በምን እንለይ አሉ? ጥሩ ጥያቄ ነው። መጀመሪያ ግን ሤራ ምንድነው? ሤረኛስ የሚለውን እንይ።

ስትም አንድም. . .

የሤራ ክፋቱ እንዲሁ'በሬ ወለደ' ከሚል ሃሳብ የሚነሳ አለመሆኑ ነው።

ዶ/ር ዮቫን ባይፎርድ አንድ ጥያቄ አላቸው፤ «ለአንድ ክስተት ከሚሰጥ አማራጭ ትነታኔ አልፎ ቁጭ ብሎ በቁም ነገር ሤራውን የሚሸርበው ማነው?» የሚል።

እያንዳንዱ ሤራ ሦስት መሠረታዊያን አሉት፡ ሤራ ሸራቢው፣ ሤራው እና ማሠራጫው መንገድ።

ሤራ ሸራቢው

ብዙ ጊዜ ሤራ ሸራቢዎች ራሳቸውን መደበቅ አይጠበቅባቸው ይሆናል ይላል ዶክተሩ። «ኢሉሚናቲ፣ ፍሪምናጦስ እና በቅርቡ የተፈጠሩት ስከልስ ኤንደ ቦንስ (የራስ ቅልና አጥንት) ማሕበረሰብ እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።»

ሸራቢዎች እንዲህ በውል ከሚታወቁት ባለፈ ትርጉማቸው ሰፋ ባለ ቃላትም ሊገለፁ እንደሚችሉ አስምሩልኝ ይላሉ ዶክተሩ። ይሄ ደግሞ የሤራው ተቀባይ ሰው ጠላት ብሎ የሚጠራው ወገን እንዲኖረው ያግዛል ባይ ናቸው።

ለምሳሌ 'ቢግ ፋርማ፤ ወይንም ትላልቅ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች፤ 'ግሎባል ኤሊት' ወይንም በግርድፉ የዓለም ምሁራን የምንላቸው እና ግዙፍ ወታደራዊ ተቋማት የሸራቢዎች ሤራ ሰለባ ናቸው።

ዕቅድ

ትልቁ የሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳብ ክፍል ዕቅዱ ነው። አንዳንድ ጊዜ ኃይልን ለመቆናጠጥ አልመው የሚነሱ ሸራቢዎች መኖራቸው የሚካድ ባይሆንም ሕልማቸው ከዚያ የዘለለ ብዙ ናቸው ይሉናል ዶክተር ዮቫን።

«ሤረኞች እውነታውን ከሰው ለመደበቅ ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዙ ያስተዋለ ሰው፤ ከበስተጀርባው አንድ ብርቱ ኃይል ያለው አካል እንዳለ መጠራጠሩ አይቀሬ ነው።»

«ዓለምን መቆጣጠር የሚለው ሐሳብ ለሤረኞች እጅግ የተመቸ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። አንድ ክስተት ሲፈጠር የምትገኘውን ቀዳዳ ተጠቅመው የሚያሤሩ በርካቶች ናቸው።»

መድረክ

የዓለም ኃያላን ምን ያህል ሊቆጣጠሩን እንደሚሹ ማስረዳት እና ከእግር ኳስ ጨዋታ በፊት ትንታኔ መስጠት መመሳሰል አላቸው። በርካታ ማስረጃዎች፣ መረጃዎች እና የ'ሊሆን ይችላል' ትንታኔዎች ይቀርባሉ። ሁሉም የመሰለውን አስተያየት ይሰጣል፤ ነገር ግን የሁሉም ያለማመን መብት የተጠበቀ ነው።

ቢሆንም ብዙዎች በመስማማት ጭንቅላታቸውን ከላይ ታች መወዝወዛቸው የግድ ነው።

ሤራ ጠንሳሾች ለማሳመን የማይቆፍሩት ድንጋይ የለም። መንግሥት፣ ሳይንስ እና መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ለሤረኞች ሽረባ የተመቹ መድረኮች ናቸው።

ዶክተር ማይክ ውድ፤ በእንግሊዙ ዊንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ልቡና ባለሙያ ናቸው። «በጭንቀት እና በሤራ ትንተና ፅንሰ-ሐሳብ መካከል ግንኙነት እንዳለ ጥናት ያሳያል» ይላሉ።

«ሰዎች ጭንቀት ላይ ባሉ ጊዜ፤ ሕይወት ከበድ በምትል ጊዜ የሤራ ፅንሰ-ሐሳብን ወደ መቀበል ያደላሉ።»

በአጠቃላይ የምሁራኑ ሐሳብ 'ክፉ ጊዜ' ለሤራ ሸራቢዎች የተመቸ ነው፤ የሚል ነው።

ምክር ቢጤ

የሤራ ፅንሰ-ሐሳብና መዘዙን ያጠኑ ሰዎች 'ፅንሰ-ሐሳቦቹ ለሰው ልጅ ጠንቅ ናቸው' ይላሉ። «ክትባት ለአእምሮ ዝግመት ያጋልጣል ብሎ በማመን ልጆቻቸውን ያላስከተቡ ሰዎች የአብራካቸውን ክፋዮች ለአደጋ እያጋለጧቸው ይሆናል እንጂ ከጉዳት እየታደጓቸው አይደለም» የሚሉት ዶ/ር ፓንታዚ ናቸው።

እርስዎ 'እኔ እንኳ በዚህ የጅል ሃሳብ አልሸወድም' ብለው የሚሉ ከሆነ በጣሙን መጠንቀቅ አለብዎ።

ዶ/ር ዮቫን «ሰዎች ብዙ ጊዜ አሁንስ ምን ዓይነት ሤራ እየተወጠነ ነው የሚለውን ለማሰስ ወደ መረጃ መረቦች ያቀናል፤ ነገር ግን በርካታ ሰዎች ማመንም አለማመንም አይሹም። እንዲሁ መሃል ላይ መገኘትን ይመርጣሉ እንጂ። ይህ ደግሞ አደጋ ነው» ሲሉ ይተነትናሉ።

እውነት የሆነውን መርምሮ መለየት አለመቻል ለሤረኞች ሠርግና ምላሽ ነው።