ልጃቸውን ወደ ፓርላማ ይዘው የመጡት አባል ከምክር ቤቱ ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Twitter
አንዲት የኬንያ ፓርላማ አባል ጨቅላ ልጃቸውን ወደ ምክር ቤት ይዘው በመምጣታቸው ከፓርላማው በግድ እንዲወጡ መደረጋቸው ተነገረ።
ዙሌካህ ሃሰን የተባሉት የፓርላማ አባል ጨቅላ ልጃቸውን ወደ ምክር ቤት ይዘው ለመሄድ የተገደዱት ችግር አጋጥሟቸው እንደሆነ ቢናገሩም ሰሚ አላገኙም።
ውይይት ላይ የነበረው የኬንያ ፓርላማ በመንግሥት በሚተዳደረው ኬቢሲ ቴሌቪዥን በቀጥታ ሲተላለፍ የቆየ ሲሆን የፓርላማ አባሏ ልጃቸውን ታቅፈው ሲገቡ ስርጭቱ ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ ነበር።
ከዚህ ክስተት በኋላ አንዳንድ አባላት ጩኽት በማሰማታቸውና ትርምስ በመፈጠሩ የፓርላማው ምክትል አፈ ጉባኤም በምክር ቤቱ ውስጥ የተፈጠረው ክስተት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር።
ምክትል አፈ ጉባኤው ልጃቸውን ይዘው የመጡትን የምክር ቤት አባል ድርጊት "ታይቶ የማይታወቅ" ነው በማለት ከስብሰባ አዳራሹ እንዲወጡ አዘዋል።
የፓርላማ አባሏ ዙሌካህ ሃሰን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከስድስት ዓመት በፊት ለልጆች የሚሆን ክፍል በፓርላማው ውስጥ እንዲዘጋጅ የተወሰነ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም ሲሉ ተናግረዋል።
"ከህጻን ልጄ ጋር ወደ ፓርላማው ላለመምጣት የቻልኩትን ለማድረግ ሞክሬ ነበር። ነገር ግን ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ስላጋጠመኝ ነው የተገደድኩት፤ ምን ማድረግ እችላለሁ?" ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።
የፓርላማ አባሏ አክለውም የህጻናት ማቆያ ቢኖር ኖሮ ይህ አይነቱ ነገር እንደማይከሰት በመጥቀስ "በርካታ ሴቶች በፓርላማው ውስጥ እንዲሳተፉ የምንፈልግ ከሆነ ምቹ ሁኔታዎች መዘጋጀት አለባቸው" ሲሉ ዙሌካህ ሃሰን ጠቅሰዋል።
በፓርላማው መመሪያ መሰረት ህጻናትን ጨምሮ አባል ያልሆኑ ሰዎች ወደ ምክር ቤቱ መግባት አይፈቀድላቸውም።
የፓርላማ አባሏ ከነልጃቸው ከምክር ቤቱ ከተባረሩ በኋላ በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ክርክር ተነስቷል።
ሌሎች ሃገራት ህጻናት ወደ ፓርላማ እንዲመጡ መፍቀዳቸውን እንደምሳሌ በማንሳት የምክር ቤት አባሏን ሲያደንቁ፤ ሌሎች ደግሞ እናትየው ይህን ያደረገችው ትኩረት ፍለጋ ነው በሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል።












