ለኬንያ ፓርላማ የተላከው ጭነት ባዶውን ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከቻይና ለኬንያ ፓርላማ በተበረከቱ ኮምፒውተሮች ተሞልቶ መምጣት የነበረበት የእቃ መጫኛ ኮንቴይነር ባዶውን ተገኘ።
የሃገሪቱ ባለስልጣናት ኮንቴይነሩን በኮምፒውተሮች ተሞልቶ እናገኘዋለን ብለው ቢጠብቁም አንድ ነጠላ ኮምፒውተር ከውስጡ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከሁሉ ግራ ያጋባቸው ደግሞ ኮንቴይነሩ ተቆልፎበት የነበረው ማሸጊያና ቁልፍ ሳይሰበር ባለበት መገኘቱ ነው።
"ባዶ ኮንቴይነር ከቻይና በመርከብ ላይ ተጭኖ እንዴት ኬንያ እንደደረሰ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው" ሲሉ የጉዳዩን ግራ አጋቢነት ለቢቢሲ የተናገሩት የሃገሪቱ የፖሊስ መርማሪ ጆርጅ ኪኖቲ ናቸው።
ከወራት በፊት በሁለቱ ሃገራት የፓርላማ አባላት መካከል የተደረገ ጉብኝትና ውይይትን ተከትሎ ኮምፒውተሮቹ ከቻይና መጫናቸውንና በሐምሌ ወር ፓርላማው እንደሚረከብ የተገለፀ ቢሆንም አሁን ግን ኬንያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በክስተቱ ግራ ከተጋቡት መካከል መሆኑን ገልጿል።
ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ "ኮንቴይነሩ ባዶውን እንደተገኘ የኬንያ ብሔራዊ ምክር ቤት ሲያሳውቀን ድንጋጤ ተሰምቶናል" ሲል ያልተጠበቀ ነገር መሆኑን ገልጿል።
አክሎም ለዓመታት የሚሰጡ ድጋፎች ያለምንም ችግር ከታሰበበት ቦታ ሲደርስ መቆየቱን ኤምባሲው ገልጾ እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥማቸው የመጀመሪያው መሆኑንም አመልክቷል።
የኬንያ የወንጀል ምርመራ መስሪያ ቤት ዋና ኃላፊ የሆኑት ጆርጅ ኪኖቲ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ከቻይና ለኬንያ ፓርላማ ተብሎ የተላከው ኮንቴይነር ውስጥ አሉ የተባሉት የእቃዎች ዝርዝር ላፕቶች፣ ኮምፒውተሮችና ሌሎች ተዛማጅ እቃዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
እነዚህ ለፓርላማው ከቻይና በእርዳታ የተሰጡት እቃዎች የት እንደደረሱ የሚጠቁም አንዳች ፍንጭ እስካሁን አልተገኘም።












