የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ ተራዘመ

የአዲስ አበባና እና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫ ከቀጣዩ ሃገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባደረገው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው ወስኗል።

ወደ 2011 ዓ.ም እንዲራዘም የተደረገውን የሁለቱን ምክር ቤቶች ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ መሰረት ማካሄድ እንደማይችል ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 4/2011ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፃፈው ደብዳቤ የሁለቱን ምክር ቤት ምርጫ እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ማካሄድ እንደማይቻል ጠቅሷል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት ያቀረበው ምርጫ አስፈፃሚዎችን ለመመልመል፣ ለማደራጀት እና ለስልጠና የቀረው የዓመቱ ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው። በውሳኔውም መሰረት በሥራ ላይ ያሉት ምክር ቤቶች ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሥራቸውን እያከናወኑ ይቀጥላሉ።

በ2010 መካሄድ የነበረበት የሁለቱ ምክር ቤቶች ምርጫ ሃገሪቱ ውስጥ በነበረው አለመረጋጋትን ተከትሎ በዚህ ዓመት እንዲካሄድ መራዘሙ የሚታወስ ነው።

ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምርጫ በሃገሪቱ ከሚካሄዱ ብሔራዊ ምርጫዎች ጋር የሚካሄድ የነበረ ሲሆን፤ አወዛጋቢውን የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ ከተማዋ በባለአደራ አስተዳደር ስር ቆይታ ምርጫ በመደረጉ የምርጫው ጊዜ ከሌሎቹ ክልሎች የተለየ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።