የኤሌክትሪክ ኃይል ለመኖሪያ ቤቶች በፈረቃ መከፋፈሉ መቅረቱ ተገለፀ

ግልገል ጊቤ ሦስት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሁለት ወራት በላይ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፈረቃ ከዛሬ ሐምሌ 1፣ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደማይኖር የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ከፈረቃ ነፃ በሆነ መንገድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚያገኙ ሲሆን ፈረቃው ግን በተለያየ ደረጃ ላይ ባሉ ኢንዱስትሪዎች ተግባራዊ እንደሚሆን ነው።

ኢንዱስትሪዎች ከሚያስፈልጋቸው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ውስጥ በቀን ግማሹን ብቻ የሚያገኙ ሲሆን ከምሽቱ አምስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ድረስ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦቱን እንደሚያገኙ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ድንጋይ የሚሰብሩ (የሚፈጩ) ማሽኖች በሚቀጥለው አንድ ወር የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይጠቀሙም እግድ ተጥሎባቸዋል።

በመላው ሃገሪቱ ሲያጋጥም የሰነበተው ኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያቱ በኃይል ማመንጫ ግድቦች ውስጥ በቂ ውሃ ባለመኖሩ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በተለይም በግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት የ476 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት እጥረት መከሰቱን መገለፁ የሚታወስ ነው።

በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ 180 ሚዮን ዶላር ታገኝበት የነበረውን የኃይል አቅርቦት አቋርጣለች።

ለሱዳን የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ፤ እንዲሁም ለጂቡቲ ከምታቀርበው ደግሞ ግማሹን ኃይል ማቋረጧን የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል።