የእንግሊዝ አምባሳደር የትራምፕ አስተዳደርን 'የፈረሰ እና የተከፋፈለ' ሲሉ ወረፉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

አፈትልከው የወጡ ኢሜይሎ በአሜሪካ የብሪታኒያ አምባሳደር የሆኑት ኪም ዳሮች የትራምፕ አስተዳደርን 'ደካማ፣ በራሱ የማይተማመን፣ ክህሎት የሌለው እና ተወዳዳሪ ያልሆነ' ሲሉ ወረፉ።

አምባሳደሩ አፈትልከው በወጡ ኢሜይሎች ላይ ዋይት ሃውስ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ስር ''የፈረሰ'' እና ''የተከፋፈለ'' ነው ብለዋል።

የብሪታኒያ የውጪ ጉዳይ ቢሮ አፈትልከው የወጡት ኢሜይሎች ''ከባድ ችግር ፈጥረዋል'' በማለት ሃሰተኛ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።

ዋይት ሃውስ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

አምባሳደሩ በተለዋወጧቸው መልዕክቶች የትራምፕ አስተዳደር ኃላፊነቱን በትክክል መወጣት መቻሉ ላይ ጥርጣሬያቸውን አስቀመጠዋል።

Sir Kim Darroch

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሰር ኪም ዳሮች

አምባሳደሩ ትራምፕ ከሳምንታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም ያደጉት የሥራ ጉብኝት ''ተደንቀዋል'' ያሉ ሲሆን፤ አሁንም አስተዳደሩ ለራስ ፍላጎት ብቻ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ''ይህ ምድር አሁንም ቅድሚያ ለአሜሪካ የሚባልበት ነው'' ሲሉም አክለዋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ከብሬክግዚት በኋላ ስለሚኖራቸው የንግድ ልውውጥ በሚመለከት ለመድረስ ላሰቡት የንግድ ስምምነት፤ በአየር ጸባይ ለውጥ፣ የመገናኛ ብዙኃን ሪፎርም እና በሞት ቅጣት ላይ ያላቸውን ልዩነት የንግድ ስምምነቱን ከግብ ለማድረስ ችግር እንደሚሆን በጽሑፋቸው ገልጻዋል።

ፕሬዝደንቱን ስታገኘው ''ጉዳይህ እንዲገባው ቀላል ማድረግ ይኖርብኃል'' በሚል አምባሳደሩ የትራምፕን አእምሮ ውስብስብ ነገሮችን ለመረዳት እንደሚሳነው የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።

ከአንድ ወር በፊት በተላከ መልዕክት ሰር ኪም ዳሮች፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ያላትን ፖሊሲ ''ወጥ ያልሆነ፣ የተጣረሰ'' ሲሉ አጣጥለውታል።

አፈትልከው የወጡት ኢሜይሎች ከ2017 ጀምሮ የነበሩ ልውውጦች መሆናቸው ታውቋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጪ ጉዳይ ቢሮ ቃል አቀባይ ''የዲፕማሎማቶች አስተያየት የሚንስትሮች ወይም የመንግሥት አቋሞች ናቸው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ እውነታውን የሚያመላክቱ እንደሆኑ አድርገን እንወስዳቸዋለን'' ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረው እንደተናገሩት ሚንስትሮች እና የመሚለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ምክሩን እና ምልከታውን ይቀበላሉ። አምባሳደሮችም ይህን መሰል አስተያየቶችን ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ ማስተላለፍ አለባቸው ብለዋል።