ዓንዶም ገብረጊዮርጊስ፡ የአሜሪካ ምክርቤት አባል ለመሆን ቅስቀሳ እያደረገ ያለው ኤርትራዊ

ዓንዶም ገብረጊዮርጊስ

የፎቶው ባለመብት, AG

የ34 አመቱ አንዶም ከኤርትራውያን እናትና ኣባት የተወለደው አሜሪካ ውስጥ ነው። የከፍተኛ ትምህርቱን በፖለቲካል ሳይንስና በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ አሜሪካ ከሚገኘው የል ዩኒቨርስቲ ተከታትሏል። ለአመታትም የማህበራዊ ፍትሕ ተሟጋች ሆኖ ሰርቷል። በኒውዮርክ ውስጥ የኮንግረስ አባል ለመሆን ቅስቀሳ የጀመረው አንዶም ከቢቢሲ ትግርኛ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ከመምህርነት ወደ ፖለቲካ እንድትገባ ምንድን ነው የገፋፋህ?

ለኤርትራ ነጻነት ከታገሉት ወላጆች በመወለዴ ከልጅነቴ ጀምሮ የፖለቲካ ግንዛቤ ነበረኝ። ስለ ኤርትራ ትግል፣ ተስፋና ተግዳሮቶች ይነግሩኝ ነበር። የአምስት ዓመት ልጅ ሆኜ ከእኩያዎቼ በተለየ መልኩ በኒውዮርክ እየሆኑ ስለነበሩ ነገሮች አውቅ ነበር። ሰለ አንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎችም እንዲሁ አውቅ ነበር። ምክንያቱም ወላጆቼ ስለእነዚህ ቦታዎች ደጋግመው ይነግሩኝ ነበር። በኢትዮጵያና ኤርትራ በተደረገው ጦርነትም አጎቴን አጥቻለሁ። ትግርኛ ቋንቋ ባልችልም፤ እነዚህ አስፈሪ የፖለቲካ ሁኔታዎች ስትሰማ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ፍላጎት ያድርብሃል። በርግጥ እዚሁ አሜሪካ ውስጥም የስደተኞች ጉዳይ፣ ሃይማኖት እንዲሁም የዘረኝነት የመሳሰሉ ችግሮች አሉብን። እነዚህ ናቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንድሆን የገፋፉኝ።

በአሜሪካ ወስጥ የሚኖሩ ታዋቂ ኤርትራውያንስ ተጽእኖ አሳድረውብህ ይሆን?

አዎ! በተለይ ጆ ንጉስ፤ ኤርትራዊ ባትሆንም ኤልሃምን ዖማርም ሌላ አርአያ የሆነችኝ ናት። ባለፈው ምርጫ በርካታ ፖለቲከኞች በየደረጃው የተለየዩ የፖለቲካ ኃላፊነቶች ሲይዙ ተመልክተናል። ጆ ንጉስ ባሸነፈበት ወቅት ለበርካታ ትውልደ-ኤርትራ አሜሪካውያን ትልቅ ዜናና መነቃቃትን የፈጠረ ጉዳይ ነበር። በርካታ የቤተሰባችን አባላትም ተራው ያንተ ነው ይሉኝ ነበር። በፖለቲካውም ተሳትፌ አስተዋፅኦየን እንዳበረክትም አስተያየቶችንም እየሰጡኝ ነው።

አጎትህን ያጣኸው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ነው፤ አሁን በሁለቱ ኃገራት መካከል የተፈጠረውን ዕርቀ ሰላም እንዴት ታያዋለህ?

ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረውን ሁኔታ ኢሳያስ እንደ ሰበብ ሲጠቀምበት ቆይቷል። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትም ሆነ ህገ-መንግስት የለም። በሁለቱ ሃገራት ሰላም ተፈጠረ ማለት ያ ማሳበብ ይቀራል ማለት ነው። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሊከበር ይገባል። ህገ መንግሥት አስፈላጊ ነው። ወጣቶችን በብሔራዊ ግዳጅ ወደ ሳዋ ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤት ሊሄዱ ይገባል። ለዚያም ነው እየተባለ ያለውን ሰላም በጥራጣሬ የማየው።

ኤርትራ ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲ እስኪሰፍንና ሰብአዊ መብቶች እስኪከበሩ ድረስ መጠራጠሬን እቀጥላለሁ።

ጋንዲም እንዳለው "ሰላም አለ የሚባለው ጦርነት ስለሌለ አይደለም። ማህበራዊ ፍትህ ሲኖር ነው"

ወደ ኤርትራ ሄደህ ታውቃለህ?

አዎ! የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ሄጄ ነበር፤ በወቅቱ ልደቴንም ያከበርኩት እዛው ነው። በህይወቴም ደስ ያለኝ ጊዜ ነበር።

ወላጆቼ በየቀኑ ስለ ኤርትራ ስለሚያወሩ፤ እኔም እንድ ልጃቸው ኤርትራን ማየት ነበረብኝ። ገና አስመራ አየር መንገዱ ላይ ወጣ እንዳልን ግራና ቀኝ ወደ ሰማይ መመልከት ጀመርኩ። በርካታ ኤርትራውያን በተለይም ሴቶች ደግሞ አበባ ይዘው ዕልል... ሲሉም ነበር። በህይወቴ እንደዚህ አይነት 'እንኳን ደህና መጣህ!' ተብዬ አቀባበል ተደርጎልኝ አያውቅም። ለእኔ ያኔ ኤርትራ የምድር ገነት ነበረች።

ከ25 አመታትም በኋላ ተመልሼ ወደ ኤርትራ የሄድኩት ከሁለት አመታት በኋላ ነው።

ለሁለተኛ ግዜ ተመልሰህ ስትሄድስ ኤርትራን እንዴት አገኘሃት?

ትግርኛ ቋንቋ አለመቻሌ ምናልባት ትዝብቴን ጎዶሎ ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን ከ25 አመታት በፊት ካየኋት ኤርትራ ፈፅሞ የተለየች ነበረች። በዛን ወቅት ይህን ያህል የውኃና የመብራት ችግር አልነበረም፤ አሁን ግን በከፍተኛ ሁኔታ የውሃና የመብራት ችግር አለ። ከዚህ ሁሉ በባሰ ሁኔታ የነበረው ተስፋ ደብዛው ጠፍቷል። አብዛኞቹ ያነጋገርኩዋቸው ወጣቶች ከአገር መውጣት እንደሚፈልጉ ነግረውኛል። ማህበረሰቡ በምን አይነት ችግር እየኖሩ ሲነግሩኝ በጣም ነው ያዘንኩት። ራሴን የማየው የማህበረሰቡ አካል አድርጌ ነው። ልዩነታችን እኔ አሜሪካ መወለዴ ብቻ ነው።

ዓንዶም ገብረጊዮርጊስ

የፎቶው ባለመብት, AG

የኮንግረስ ውድድሩን ካሸነፍክ ለኤርትራ ምን ለመስራት ታስባለህ?

ኤርትራ ለምንም አይነት ሁኔታ ከተዘጉ አገሮች መካከል ነች። መሪው ከተናገረው ውጪ አንዳች ነገር ትንፍሽ ካልክ የምትታሰርበት አገር ነው። አሜሪካ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ የተለያዩ አገሮች ላይ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን መምሰል እንዳለበት ያሳስባታል።

የኤርትራም ጉዳይንም የማየው በዚሁ መንገድ ነው። ነፃ ፖለቲካዊ አስተዳደር፣ ሰብአዊ መብት እንዲከበርና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ያስፈልጋል። አሜሪካ ውስጥ ያሉ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎችም የጀመሯቸው የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አሉ የነሱንም እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ እገፋበታለሁ።

የምርጫ ቅስቀሳው እንዴት እየሄደ ነው ? አሸንፋለሁ ብለህ ታምናለህ?

ቅስቀሳ ከጀመርኩ አንድ ሳምንቴ ነው። በጥሩ እየሄደ ነው፤ መልእክቶቻችን እያስተላለፍን ነው። በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄድ የመጀመርያ ደረጃ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እየተንቀሳቀስን ነው። መራጮቻችን ምን ሃሳብ እንዳለን እያስተዋወቅን እንገኛለን።

በሚቀጥለው ዓመት ሁለተኛ ኤርትራዊ በአሜሪካ ምክርቤት ይኖራል ብየ አምናለሁ።

የምትወክለው አካባቢ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በብዛት የሚኖሩበት ነው?

እኔ የምወክለው አካባቢ የተለያዩ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ነው፤ ይሁን እንጂ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚገኙበት አይደለም።

ዚደንት ዶናልድ ትራምፕን እንዴት ታያቸዋለህ?

ፕረዚዳንት ትራምፕ ከመመረጣቸው በፊትም ሆነ በኋላ ንግግራቸው ዘረኝነትን የሚያንፀባርቅ እንዲሁም የአንዱን ፆታ የበላይነት የሚሰብክ ነው። ይሄ አሜሪካውያንን የሚከፋፍል ነው።

የትራምፕ መምጣት የፈጠረው አዎንታዊ ነገር ካለ ህዝቡን አንድ ላይ ማምጣት ችሏል።

ዲሞክራቶችን ወክለው በፕንታዊ ምርጫ እየተሳተፉ ካሉት የትኞቹን ነው የምትደግፈው?

ዲሞክራቶችን ወክለው የሚወዳደሩ ብዙ ናቸው። የእግር ኳስ ቡድን ያክላሉ። [ሳቅ] በአንድ በኩል ጥሩ ነው። ምክንያቱም የተለያዩ ሃሳቦችን ስለሚያመነጩ አማራጭ ይሰጣል። በመጀመሪያ የምደግፈው በርኒ ሳንደርስ ነበር። አሁንም እደግፈዋለሁ።

ይሁን እንጂ አሜሪካን በሚቀይሩና ትኩረት የተነፈጉ ማህበረሰቦች በሚጠቅሙ ፖሊሲዎችዋ ኤሊዛበት ዋረንም ቀልቤን እየሳበቸው ነው።