ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ ፍላጎቱን ያሳየው የሳፋሪኮም ሥራ አስፈጻሚ አረፉ
በምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ስኬታማውና በኢትዮጵያ ገበያም ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳየው ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ቦብ ኮሊሞር ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ድርጅታቸው አስታደቀ።
ሳፋሪኮም የዋና ሥራ አስፈጻሚውን ዜና እረፍት ይፋ ባደረገበት መግለጫው ላይ እንዳመለከተው፤ ቦብ ኮሊሞር በ61 ዓመት እድሜያቸው በካንሰር ምክንያት ዛሬ ጠዋት ቤታቸው ውስጥ ህይወታቸው ማለፉን ገልጿል።
ቦብ ካሊሞር የካሪብያኗ ጉያና ሃገር ተወላጅ ሲሆኑ በዜግነት ደግሞ እንገሊዛዊ ነበሩ።
ከሁለት ዓመት በፊት ጥቅምት ወር ላይ ቦብ ኮሊሞር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሄደው ላጋጠማቸው የደም ካንሰር አይነት ለወራት ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ሥራቸውን ማከናወን ቀጥለው እንደነበር ድርጅታቸው በመግለጫው ጠቅሷል።
ከዚያም በኋላ ህክምናቸውን ሲከታተሉ እንደቆዩ ነገር ግን የጤና ሁኔታቸው "ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር" ሲል አስታውሷል።
ቦብ ኮሊሞር የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲሆን፤ በቆይታቸውም በሞባይል ስልክ ክፍያን መፈጸምን ጨምሮ ድርጅቱ በአካባቢው ሃገሮች ውስጥ ያለውን የመሪነት ደረጃ ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ አስችለውታል።
የቦብ ኮሊሞር ህልፈትን ተከትሎ በመላው ኬንያ ያሉ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ሃዘናቸውን እየገለጹ ሲሆን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ግለሰቡ "ባለራዕይና የተለዩ መሪ ነበሩ" ሲሉ ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ደግሞ "ምሳሌ የሚሆኑ፣ ብልህና ደፋር" ሲሉ በሃዘን መግለጫ መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉን ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንደምታደርግ ካሳወቀችበት ጊዜ ጀምሮ ሳራፊኮም በዘርፉ ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን ከገለጹ ቀዳሚ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው።