አሜሪካ፡ ብዙ ሰዎች በፌሰታል የተጣለችውን ልጅ በጉዲፈቻ ለመውሰድ እየጎረፉ ነው

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, በአሜሪካ በጆርጅያ ግዛት በፌስታል የተጣለችው ሕፃን ልጅ

በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት በፌስታል ተጥላ የተገኘችውን ህፃን ወስዶ ለማሳደግ በዓለም ዙሪያ ያሉ ቤተሰቦች ወረፋ መያዛቸውን የመንግሥት ኃላፊዎች ተናገሩ።

'ኢንድያ' የሚለው ቅፅል ስም የወጣላት ሕፃን ከ20 ቀናት ገደማ በፊት በፌስታል ተጠቅልላ የተገኘች ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቅሶዋን ሰምተው ነበር ለፖሊስ ደውለው ያሳወቁት።

ፖሊሶች በደረት ካሜራቸው በቀረፁት ተንቀሳቃሽ ምስል ፌስታሉን ቀደው ሲያወጧት ይታያል።

ሕጻኗ ወዲያው ወደ ሆስፒታል የተወሰደችው ሲሆን ዶክተሮች ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ተናግረው በአሁን ሰዓትም ኪሎዋ እየጨመረ መሆኑን አሳውቀዋል።

ከተገኘች ሦስት ሳምንታት የሞላት ሕፃኗ በሕፃናት ማቆያ የምትገኝ ሲሆን 'ደስተኛ' እና 'በጥሩ ሁኔታ ላይ' ትገኛለች ተብሏል።።

ቋሚ መኖሪያ ቤት እስኪገኝላት ድረስ በሕፃናቱ ማቆያ እንደምትቆይ የተነገረ ሲሆን የፎርሲት ክልል የፖሊስ ኃላፊ ቢሮ የልጅቷን እናትና ዘመዶች ለማግኘት እየጣሩ ነው።

ፖሊስ በፌስቡክ 'ስለ ህፃኗ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው' አሳውቀዋል።

ቶም ሬሊንግ የጆርጅያ የቤተሰብ እና ሕፃናት አገልግሎት ዳይሬክተር ሲሆን ሕፃኗን ለማሳደግ ደግሞ ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ቤተሰቦች አሉ ይላል።

ቶም "ልጅቷን ለማሳደግ እየተረባረቡ ያሉ ቤተሰቦች ወረፋ ይዘዋል" በማለት ለኤቢሲ የቴሌቪዥን ጣቢያ 'ጉድ ሞርኒንግ አሜሪካ' ፕሮግራም ተናግሯል።

በጆርጅያ ፖሊስ የተገኘችው ኢንድያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጫካ አካባቢ ለቅሶ የሰሙ ነዋሪዎች ለፖሊስ አሳወቁ

በአስገራሚ ሁኔታ የተገኘችው ይህች ሕፃን ሁኔታው በዓለም ዙሪያ ያሉ የብዙኃን መገናኛዎችን ትኩረት እንድትስብ አድርጎ በመቶ የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ልጅቷን በጉዲፈቻ ለማሳደግ ፈቃደኝነታቸውን አሳውቀዋል።

ቶም ሕፃኗ በሕይወት መኖሯ ሲያስብ "እንደዚህ ዓይነት ተዓምራዊ ክስተት በሕይወቴ አይቼ አላውቅም" ብሏል።

እትብቷ እምብርቷ ላይ እንዳለ የተገኘችው ሕፃን በፌስታል ውስጥ ተጥላ በአካባቢው ነዋሪዎች ስትገኝ ከተወለደች ሰዓታትን ብቻ ነበር ያስቆጠረችው።

የክልሉ ፖሊስ ኃላፊ ሮን ፍሪማን የሕፃኗን መትረፍ "የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት" እንደሆነ ገለፀዋል።