የጄነራል ሰዓረ ቀብር አዲስ አበባ ሳይሆን መቀሌ ይፈጸማል

ጀኔራል ሰዓረ መኮንን

የፎቶው ባለመብት, ETV

ቅዳሜ ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት የሃገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የጄኔራል ሰዓረ መኮንን አዲስ አበባ ውስጥ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቀብራቸው እንደሚፈጸም የተነገረ ቢሆንም ከቤተሰቦቻቸውና ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት እንደተነገረው ሥነ ሥርዓታቸው መቀሌ ውስጥ እንደሚፈጸም ተገለጿ።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ቀደም ብሎ እንደተናገሩት የጄነራል ሰዓረ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ ዕለት እንደሚፈጸምና በዚህም የጄነራሉ አስከሬን ከቤታቸው ተነስቶ በወታደራዊ ሥርዓት ታጅቦ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ተወስዶ ከጠዋት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ በሚሊኒየም አዳራሽ ቤተሰቦቻቸው፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በሚገኙበት የሽኝት ሥነ ሥርዓት ይደረጋል ተብሎ ነበር።

ነገር ግን ሰኞ ከሰዓት በኋላ የጄነራሉ ቤተሰቦችና የትግራይ የክልል ሕዝብና መንግሥት ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ የጄነራሎቹ ቀብር መቀሌ ውስጥ እንደሚፈጸምና ይህን ሥነ ሥርዓት የሚያስተባብር ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዠንም የጄነራል ሰዓረ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቀሌ እንደሚካሄድ እና ማክሰኞ ጠዋት ቦሌ የሽኝት ሥነ ሥርዓት እንደሚደረግ ግልጸዋል።

ከጄነራል ሰዓረ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደሉት የጄኔራል ገዛኢ አበራ ቤተሰቦች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት አስከሬናቸው ወደ ትውልድ ስፍራቸው ተወስዶ የሚቀበር መሆኑንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ተናግረዋል።

ሁለቱ ጄነራል ሰዓረ መኮንንና ጄነራል ገዛኢ አበራ ቅዳሜ ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ አዲስ አበባ በሚገኘው የጄነራል ሰዓረ ቤት ውስጥ በጄነራሉ ጠባቂ መገደላቸው መገለፁ ይታወሳል።