በምስራቅ ጎጃም መነኩሴው ለምን በቁጥጥር ሥር ዋሉ?

የፎቶው ባለመብት, Awabel woreda Communication
ከትናንት በስቲያ ሚያዚያ 28 ቀን 2011 ዓ. ም. በምስራቅ ጎጃም ዞን፤ አዋበል ወረዳ በምትገኘው እነጋትራ ሐና ገዳም አስተዳዳሪ አባ ገ/ሥላሴ ሳሙኤል ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተፈጠረ ግጭትን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የወረዳው ባለስልጣናት ለቢቢሲ አስታወቁ።
የወረዳው አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ይሄነው አበባው ከመነኩሴው ጋር 7 የጦር መሣሪያዎች የተያዙ ሲሆን፤ ስድስቱ ለገዳሙ መጠበቂያ ተብሎ ከመንግሥት ወጭ ተደርጎ የተሰጣቸው ነው ይላሉ፤ ይሁን እንጂ ሕጋዊ ያልሆነ አንድ ሽጉጥ የተገኘባቸው መሆኑን ገልፀዋል።
"ስድስቱ መሣሪያዎች ከመንግሥት ወጭ ተደርገው ይሰጡ እንጂ በማን ሥም እንደተመዘገቡ ገና እየተጣራ ነው" ሲሉ ኃላፊው አክለዋል።
ኃላፊው የገዳሙ አስተዳዳሪ ከዚህ ቀደምም ከኅብረተሰቡ ጋር ቅራኔ ነበራቸው ሲሉ ይገልፃሉ።
"ሌላ የኃይማኖት መገልገያ ቦታ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ማንኛውንም የኃይማኖት አገልግሎት የሚያገኙት እዚያ ነበር፤ እኚህ ግለሰብ ወደ ገዳሙ ከገቡ ጀምሮ ሕዝቡ ወደ ገዳሙ እንዳይገባ መከልከሉን ኅብረተሰቡ ቅሬታ ሲያሰማ ቆይቷል" ይላሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊው አቶ ይሄነው።
ለገዳሙ ተብሎ ከተፈቀደው መሬት ውጭ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አስፋፍቶ ይዟል፤ በኃይል ነጥቆናል የሚሉ ቅሬታዎችንም ኅብረተሰቡ ሲያሰማ መቆየቱን ያክላሉ።
ከትናንት በስቲያ የተፈጠረው ግጭትም መነሻው እነዚሁ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መሆናቸውን አቶ ይሄነው ገልፀውልናል።
ግጭቱ የተፈጠረበትን ምክንያት ሲናገሩም፤ "በኅብረተሰቡ ቅሬታ ያሳደረውን መሬት ለማረስ መነኩሴው በሬዎች ይጠምዳሉ፤ ከዚያ በኋላ መሬቱ አይታረስም ከሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጠረ" ይላሉ።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መንግሥት ቢጋርም በበኩላቸው ቦታው 'የወል መሬት' ሲሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ ታቦት ሲወጣ የሚያከብሩበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደምም መነኩሴው ቦታውን አርሰው እንዳመረቱበት የሚናገሩት አስተዳዳሪው፤ ኅብረተሰቡ ቅሬታ በማሰማቱ ሰብሉን ለጋራ እንዳደረጉት ያስታውሳሉ።
አቶ መንግስት እንደሚሉት መነኩሴው ከእምነት ውጭ የሚያከናውኗቸው ተግባራት አሉ ሲሉም ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎችን ኅብረተሰቡ ሰንዝሯል።
እስካሁን ድረስ የኅብረተሰቡ ጥያቄ ለምን ምላሽ ሳይሰጠው ቆየ? ስንል የጠየቅናቸው አስተዳዳሪው፤ በአካባቢው ማኅበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ባለፉት ወራት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ጋር እርሳቸው ባሉበት ውይይት እንደተደረገ ይናገራሉ።
በዚህ ጊዜም መስተካከል አለባቸው ያሏቸው ስድስት ጉዳዮችን ከመነኩሴው ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይናገራሉ።
ከእነዚህም መካከል ሥርዓተ ቀብር እንዲካሄድ፣ ቅዳሴ እንዲፈፀም፣ ሰበካ ጉባዔ እንዲኖረው፣ ምክትል ሊቀመንበርና የገንዘቡን ፍሰት የሚያስተዳድር አካል እንዲኖረው እንዲሁም መነኩሳት ተቀጥረው እንዲቀድሱ የሚሉ ነበሩ።
ባሳለፍነው የካቲትና መጋቢት ወር ላይ ሕጉን በመከተል እንዲሠሩና ሕዝቡም አገልግሎቱን እንዲያገኝ ውሳኔ እንደተላለፈ ይገልፃሉ።
መነኩሴው ለ28 ዓመታት በገዳሙ ውስጥ የኖሩ መሆናቸው የሚጠቅሱት የወረዳው የአስተዳደርና የፀጥታ ኃላፊ አቶ ይሄነው " መነኩሴው ገዳም ስለሆነ ማንኛውም ሰው ኃይማኖታዊ አገልግሎት ማግኘት አይችልም የሚል አቋም አላቸው" ይላሉ ።
በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ ሌላ የኃይማኖት ተቋም የለም፤ የት እንሂድ? አለበለዚያ ሌላ ቤተክርስቲያን ሊሠራልን ይገባል የሚል ጥያቄም ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ያክላሉ።
በዚህ አለመግባባት ምክንያትም የአካባቢው ማኅበረሰብ ሰው ሲሞት ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች በመሄድ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚያስፈፅሙ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ከእሳቸው ጋር የሚቀራረቡና እሳቸውን የሚደግፉ ሰዎች በገዳሙ ውስጥ ኃይማኖታዊ አገልግሎት ያገኙ ነበር፤ ሲሞቱም የሚቀበሩት እዚያው ገዳሙ ውስጥ ነው፤ ይህም በኅብረተሰቡ መካከል መከፋፈልን ፈጥሯል ይላሉ አቶ ይሄነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መነኩሴው ከሕዝቡ ጋር በሚያጨቃጭቃቸው መሬት ላይ ለማረስ በሬዎቻቸውን ጠመዱ ይላሉ።
በዚህ ጊዜ ኅብረተሰቡ ማረስ የለባቸውም ሲል ተቃወመ፤ እንዲያውም 'አንፈልጋቸውም ይውጡልን' የሚል ጥያቄ ማሰማታቸውን ይገልፃሉ።
በመሀል ከማን እንደሆነ ባልታወቀና ከገዳሙ ውስጥ በተተኮሰ ጥይት የአካባቢው ነዋሪ የሆነ የ22 ዓመት ወጣት እንደቆሰለ ያስረዳሉ።
በግጭቱ በገዳሙ ውስጥ ያሉት 10 በጭቃ የተሰሩ ቤቶችም የተቃጠሉ ሲሆን፤ አምስት ትንንሽ የዕቃ ማስቀመጫ ቤቶችም በከፊል ተቃጥለዋል። በገዳሙ ውስጥ በተቃጠሉ ቤቶችና በቆሰለው ልጅ ምክንያት ምርመራ ለማድረግ ሲባል መነኩሴው በቁጥጥር ሥር ውለው እየተጣራ መሆኑን ነግረውናል።
'ኅብረተሰቡ ከእኔ ጋር የማይስማማው ከሌላ ብሔር ስለመጣሁ ነው' የሚል ቅሬታ በመነኩሴው ይነሳ እንደነበር የጠየቅናቸው አቶ ይሄነው፤ "አስተዳደሩ ከየትም ይምጣ ከየት? ሕጋዊ ሆኖ መቆየት አለበት የሚል አቋም ነው ያለን" ይላሉ። ።
ነገር ግን መነኩሴው ያለመግባባት ችግር ነበረባቸው የሚሉት ኃላፊው በዚህም ምክንያት ከኅብረተሰቡ ጋር በሚፈጠር ግጭት 'ከሌላ ብሔር ስለመጣሁ ነው' የሚል ቅሬታ ያሰማሉ" ብለዋል።
አክለውም ግለሰቡ ለ28 ዓመታት በሠላም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የኖሩ ሲሆን፤ ከየት ብሔር እንደመጡም የሚታወቅ ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።
"በአሁኑ ሰዓት ገዳሙ ሌላ ችግር እንዳይደርስበት በፀጥታ ኃይሉ እየተጠበቀ ሲሆን፤ ከሚመለከታቸው የኃይማኖት አባቶች ጋርም እየተነጋገርን ነው፤ ባለቤት የሆነ አካል ንብረቶችን እንዲረከብ ጥረት እየተደረገ ነው" ሲሉ ገልፀዋል።
በገዳሙ የዚያው አካባቢ የሆኑ ሦስት መነኮሳት የነበሩ ሲሆን እነርሱም ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Awabel Wereda Communucation
መነኩሴው የገዳሙ አስተዳዳሪ እንዴት ሆኑ?
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምስራቅ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀብርሃናት ካህሌ በቃሉ በገዳሙና በኅበረተሰቡ መካከል የሚነሳ የቆየ አለመግባባት ነበር ይላሉ።
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የገዳሙ አባቶችንና የወረዳው ኃላፊዎችን አሰባስበው ይህንን አለመግባባት ለመፍታት እንደሞከሩ ይናገራሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ገዳሙ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የተመሠረተ ሲሆን ሁሉም ሕዝብ ይገለገልበት የነበረ ቤተክርስቲያን ነበር። እኝህ አባት ከተመደቡ ጀምሮ ወደ ገዳምነት ተቀይሮ በአንድነት ገዳም እንዲተዳደር የሚል ውሳኔ አግኝቷል።
ቤተ ክርስቲያኑ ወደ ገዳም ሲቀየር ሀገረ ስብከት ውሳኔ ያሳረፈበት ሳይሆን ከመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት በቀድሞ በነበሩ አባቶች ውሳኔ መነኩሴው እንደመጡ የሚያመለክት መረጃ እንዳገኙም ያስረዳሉ።
ሊቀብርሃናት ካህሌም ይህንኑ ሀሳብ ሲያፀኑ "የዞንም ሆነ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ከዚህ ቀደም ገዳሙ ይመራ የነበረው እዚህ አካባቢ ባሉ ባለሥልጣናት አለመሆኑን አያውቁም " ይላሉ።
ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ሰው በፍርሃት ወደ ገዳሙ ደፍሮ እንደማይገባ አስረድተው "ቦታው የሚታወቅበት፤ ነገር ግን አስተዳደሩ በውል የማይታወቅበት ደረጃ ላይ ነበር " ብለዋል።
አሁን ግን ሕዝቡ ሲወያይ "የሠራነው ቤተክርስቲያን ነው፤ የፈለግነውን አገልግሎት ማግኘት አለብን፤ የገዳሙ አስተዳዳሪ ለሚፈልጉት ሰው አገልግሎት ይሰጣሉ፤ ሌላውን ያባርራሉ" ሲል ቅሬታ ማሰማታቸውን ይናገራሉ።
ከውይይቱ በኋላ ሀገረ ስብከቱ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።
ገዳሙ የአንድነት ገዳም ከሆነ መስፈርቱን ማሟላት አለበት፤ በርካታ መናኒያን መኖር አለባቸው፤ ገዳም ቢሆንም ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት አለበት የሚል ነበር ውሳኔው።
በመሆኑም ይህም ገዳም ሰበካ ጉባዔ ተቋቁሞለት፤ የሰበካ ጉባዔ አባልነት ክፍያ እየተከፈለ፤ ህዝቡ የራሱን ተመራጮች አድርጎ እንዲገለገል ተወስኗል።
ከዚህ በኋላ የወረዳው ቤተ ክህነት ሠራተኞች የሰበካ ጉባዔ ሊመሰርቱ በሚሄዱበት ጊዜ ምዕመኑ 'እኚህ አባት ካልተነሱ አንመርጥም' ሲሉ ተቃወሙ።
"ግለሰቡ ራሳቸውን የቻለ ልዩ ባህሪ ሊኖርባቸው ይችል ይሆናል" የሚሉት ሥራ አስኪያጁ መነኩሴው የተለያዩ ቦታዎች እየሄዱ፣ እየለመኑ ገንዘብ በመሰብሰብ ገዳሙን እዚህ አድርሰውታል፤ ያስተዳድሩት ተብሎም ነበር። ሕዝቡ ግን አልተስማማም።
ከትናንት በስቲያም በተነሳው ግጭት ሕዝቡ በጡሩምባ ተቀሳቅሶ በመውጣት በገዳሙ የሚገኙ የፀበልተኞችን ቤት እንዳቃጠሉና አንድ ሰውም በጥይት መቁሰሉን እንደሰሙ ነግረውናል።
ለጥበቃ የተሰጠ መሳሪያ እንዳለ እንደሚያውቁ የተናገሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መሳሪያዎቹ እውቅና እንደተሰጣቸውና በየዓመቱ ቆጠራ እንደሚያደርጉ ሰዎቹ ሲገልፁ እንደነበር እንደሰሙ አስረድተዋል።
መነኩሴውም ከ30 ዓመታት በፊት በቦታው የተመደቡ ስለሆነ በሀገረ ስብከቱ ደረጃ የተመደቡበት ህጋዊ ደብዳቤ አላገኘንም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ከህብረተሰቡ ጋር ካላቸው ቅራኔ በስተቀር ቦታውን ለውጠውታል ሲሉ ይመሰክራሉ።












