አሜሪካ የግብፁ ሙስሊም ብራዘርሁድን በአሸባሪነት ልትፈርጅ ነው

ትራምፕና አል ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, MANDEL NGAN/Getty

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የግብፁን ሙስሊም ብራዘርሁድ አሸባሪ ድርጅት ብሎ ለመፈረጅ በዝግጅት ላይ መሆኑን ዋይት ሀውስ ትናንት በመግለጫው አስታውቋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ይህ ድርጅት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ በድርጅቱና በአባላቱ ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማእቀቦች የሚጣሉ ይሆናል። አሜሪካ ሙዝሊም ብራዘርሁድን በአሸባሪነት ለመፈረጅ የወሰነችው ከሶስት ሳምንታት በፊት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ አሜሪካን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ነው።

መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ዶናልድ ትራምፕ ይህን እንዲያደርጉ አል ሲሲ ጠይቀዋቸዋል። ትራምፕና አል ሲሲ መገናኘታቸውን ተከትሎ ትራምፕ ወዲያው ሙስሊም ብራዘርሁድ ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ መጣል የሚቻልበትን መንገድ እንዲፈልጉ የደህንነትና የዲፕሎማሲ አማካሪዎቻቸውን አዘውም ነበር።

ትናንት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ የትራምፕ አስተዳደር በውሳኔው እየገፋበት እንደሆነ አስታውቀዋል።

"ፕሬዝዳንቱ ከደህንነት አማካሪዎቻቸው እንዲሁም ከአካባቢው መሪዎች ጋር በጉዳዩ ላይ መክረዋል። እናም ይህ ውሳኔ በዚያ መሰረት እየተኬደበት ያለ ነገር ነው" ብለዋል ሳንደርስ በመግለጫቸው።

በ2013 የጦር ሃይል አዛዥ የነበሩት አል ሲሲ የሙዝሊም ብራዘርሁዱን ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ሙርሲን ከስልጣን አስወገዱ

የፎቶው ባለመብት, Spencer Platt/Getty

የምስሉ መግለጫ, በ2013 የጦር ሃይል አዛዥ የነበሩት አል ሲሲ የሙስሊም ብራዘርሁዱን ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ሙርሲን ከስልጣን አስወገዱ

እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 የግብፅ ጦር አዛዥ የነበሩት አል ሲሲ በወቅቱ ፕሬዝዳንት የነበሩትን የሙስሊም ብራዘርሁዱ ሞሃመድ ሙርሲን በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ማውረዳቸው የሚታወስ ነው። ሙርሲ ከስልጣን ከተነሱ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት መታሰራቸውም ይታወቃል።

የአሁኑ የአሜሪካ ፍረጃ ይፋ ከተደረገ ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦችና ኩባንያዎች ላይ የኢኮኖሚና የጉዞ ማእቀቦች ተግባራዊ ይሆኑባቸዋል።

ሙስሊም ብራዘርሁድ ዋይት ሃውስ ምንም ይበል ምን በእንቅስቃሴው ፀንቶ እንደሚቀጥል በድረ ገፁ ላይ ማስፈሩን ሮይተርስ ዘግቧል።

በሌላ በኩል የኒዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ደግሞ ውሳኔው በዋይት ሃውስ ባለስልጣናትና በፔንታጎን ሃላፊዎች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል።