ዕጽ በማዘዋወር የተጠረጠረችው ናይጄሪያዊት ከሳኡዲ እስር ቤት ተለቀቀች

ባለፈው ዓመት ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ በእጽ ማዘዋወር ተጠርጥራ በእስር ላይ የነበረች አንዲት ናይጄሪያዊት ተማሪ በነጻ መሰናበቷን የሃገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።

ዛይነብ አሊዩ 2000 እሽግ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን ወደ ሳኡዲ አረቢያ ይዘሽ ገብተሻል የሚል ክስ ነበር በወቅቱ የቀረባበት።

የናይጄሪያ ባለስልጣናት ግን በምርመራ ደረስንበት ባሉት መረጃ መሰረት የአሊያ ሻንጣ ውስጥ መድሃኒቶቹን በስውር ያስቀመጠው በህገወጥ የእጽ ዝውውር ላይ የተሰማራ አንድ የወንጀለኞች ቡድን ነው።

በኢስላማዊ ህግ በምትተዳደረው ሳኡዲ አረቢያ የእጽ ዝውውር ከባድ ወንጀል ሲሆን ይህንን ሲፈጽም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ የሞት ፍርድ ነው የሚጠብቀው።

ባሳለፍነው ወርም አንዲት ናይጄሪያዊ የፓኪስታንና የየመን ዜግነት ካላቸው ሰዎች ጋር በዚሁ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው በመካ ከተማ የሞት ፍርዱ ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል።

ዛይነብ አሊዩ ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለችበት ቀን ጀምሮ ብዙ ናይጄሪያውያን ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበረ ሲሆን ዛይነብ ነጻ ትሁን የሚል እነቅስቃሴ በማህበራዊ ሚዲያዎችም ጀምረው ነበር።

ማክሰኞ ዕለትም በመቶዎች የሚቆጠሩ የማይታማ ሱሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ካኖ በተባለችው ከተማ በመሰባሰብ ዛይነብ ትለቀቅ የሚል የተቃውሞ ድምጻቸውን ካሰሙ በኋላ ነው የመለቀቋ ዜና የተሰማው።

ሰኞ ዕለትም የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሞሃመዱ ቡሃሪ የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጉዳዩን እንዲከታተሉት ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር ተብሏል።

ባሳለፍነው የአውሮፓውያኑ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ዛይነብ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ሳኡዲ ተጉዛ ሆቴላቸው ውስጥ እያሉ ነበር በሳኡዲ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለችው።

እስከ ማክሰኞ ድረስም በእስር ላይ ነበረች።

የሳኡዲ ባለስልጣናት እንደገለጹት የአሊዩ ስም ያለበት ሻንጣ ኤርፖርት ውስጥ የተገኘ ሲሆን 2000 እሽግ ትራማዶል የተባለ የህመም ማስታገሻ በውስጡ ተገኝቷል።

በቅርቡ የናይጄሪያ የእጽ ቁጥጥር ኤጀንሲ እንደገለጸው በእጽ ማዘዋወር ስራ ላይ የተሰማሩ ብዙ የወንጀለኛ ቡድኖች ያሉ ሲሆን ባላወቀችው መንገድ ዛይነብም የነዚህ ቡድኖች መጠቀሚያ ሆናለች።

የዛይነብ ወላጅ አባት በሳኡዲ ስለተፈጠረው ነገር ለናይጄሪያ ፖሊስ ባሳወቁ ወቅት ልጃቸው ከናይጄሪያ ስትወጣ በተጠቀመችው ማላም አሚኑ አለማቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ምርመራ ተጀመረ።

በምርመራውም ስድስት የአየር መንገዱ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ ሲሆን በከፍተኛ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል ተብሏል።

ዛይነብ አሊዩም ወንጀለኛ አይደለሽም ወደቤትሽ መመለስ ትችያለሽ ተብላ በነጻ ተሰናብታለች።