ደስታን ለመፍጠር የሚረዱ አምስት መንገዶች

ዛሬ መጋቢት 11 ዓለም አቀፍ የደስታ ቀን ነው። በዕለት ከለት ህይወታችን ውስጥ የተለያዩ ገጠመኞች ደስታን ይሰጡናል። ነገር ግን በአጋጣሚዎች ብቻ ሳይሆን አስበንበት ደስታን መፍጠር እንደምንችል ባለሙያዎች እናገራሉ።

ይህም ልክ እንደ እስፖርተኞችና ሙዚቀኞች ሁልጊዜም ደስታም ልምምድና የትግበራ ቅደም ተከተል ያስፈልገዋል። በሂደትም የሚፈልጉትን አይነት ደስተኛ ሰው ይሆናሉ።

"ደስተኝነት ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ይልቁንም ራሳችንን ለደስታ በማዘጋጀትና በማለማመድ የምናመጣው ነው" ይላሉ በአሜሪካ ያሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ አዕምሮ ፕሮፌሰሯ ላውሪ ሳንቶስ።

በርግጥ ቀላል ላይሆን ይችላል ነገር ግን ደጋግሞ በመለማመድ ውጤታማ መሆን ይቻላል ባይ ናቸው ፕሮፌሰሯ። ለዚህም ያግዝ ዘንድ የሚከተሉትን አምስት መንገዶች በመጠቀም በተማሪዎቼ ላይ ውጤት አምጥቼባቸዋለሁና እነዚህን መከተል ተገቢ ነው ብለዋል።

1.ረኩባቸውን ተግባራት በዝርዝር መያዝ

በሥራም ይሁን በማንኛዉም አጋጣሚ ያገኟቸውን ስኬቶች በእያንዳንዱ ቀንና ሳምንት በመዘረዝር ከእነዚህ ስኬቶች የሚያገኟቸውን እርካታዎች ማጣጣም ያስፈልጋል።

2.በደንብ እና በተሻለ ሁኔታ መተኛት

ማንኛውም ደስተኛ መሆን የሚፈልግ ስው በቀን ቢያንስ 8 ስዓት መተኛት ይኖርበታል። በርግጥ ከሁሉም የደስታ መለማመጃ መንገዶች መካከል ተማሪዎች ይህን ለመተግበር እንደሚቸገሩ ፕሮፌሰሯ ይገልጻሉ። ዝምብሎ ሲታይ ቀላል ሊመስል ይችላል ነገር ግን በቂ እንቅልፍ ማግኘት ድብርትን በመቀነስና የደስተኝነትን ስሜት በመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

3. ለተወሰነ ደቂቃ የፅሞና ጊዜ መውሰድ

በቀን ቢያንስ የ10 ደቂቃ ፅሞና ማድረግ ይኖርብናል። ፅሞና ማድረግ ሙሉ ትኩረትን በመሰብበስብ ለአፍታ ከራስ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ቀጣይ በምን ነገሮች ላይ ደስታን ማምጣት እንደሚቻል መንገዱን ክፍት አድርጎ ያሳያል።

4.ከቤተሰብና ጓደኛ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ

በህይዎታችን ቅድሚያ የምንሰጣቸውንና ጤናማ ግንኙነት ካለን ሰዎች ጋር ጊዜ ሰጥተን ማውራትና መጫወት ተጨማሪ ደስታ ያመነጫል። ነገር ግን ጊዜው መብዛት እንደሌለበት ፕርፌሰር ሳንቶስ ይመክራሉ። ምክንያቱም ጊዜው በበዛ ቁጥር ከነዚህ ሰዎች ጋር ጥገኛ የመሆን እድላችን ሊሰፋ ይችላልና ነው።

5.የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን መቀነስና ብዙ የራ ግንኙነት መመስረት

ማህበራዊ ሚዲያ የሃሰት ደስታ ሊሰጠን ይችላል፤ በመሆኑም በዚህ ድርጊት ላለመደበር አጠቃቀማችንን መቀነስ ያስፈልጋል። በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በብዛት በተለይ ኢንስታግራም የሚጠቀሙት ትንሽ የመደሰት እድል ሲኖራቸው የማይጠቀሙት ደግሞ የተሻለ ደስታ እንዳላቸው ተረጋግጧል።

በአጠቃላይ በህይወትዎ ደስተኛ መሆን ከፈለጉ በምስጋና ይጀምሩ፣ ጥሩ የእንቅልፍ ሌሊት ይኑረዎ፣ የፅሞና ጊዜ ይኑርዎ፣ ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ጊዜ የያሳልፉ እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምዎን ያስተካክሉ።

ፕሮፌሰር ሳንቶስ እነዚህን መንገዶች በተማሪዎቻቸው ላይ ተግብረውት ውጤት እንዳመጡ ይናገራሉ። ለእርሰዎም ደስታ ሊያስገኝልዎ ስለሚችል ይሞክሯቸው።