ፕሬዚዳንት ማክሮ አዲስ አበባ ገብተዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ፕሬዚዳንት ማክሮ

የፎቶው ባለመብት, Office of the prime minister Twitter page

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ዛሬ መጋቢት 3 ቀን ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በላሊበላ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ለፕሬዚዳንቱ ይህ የኢትዮጵያ ጉብኝት የመጀመሪያቸው ነው።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከጎበኙ በኋላ ጉዟቸውን ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።

በላሊበላ ቆይታቸው አጠር ያለ ንግግር ያደረጉት ማክሮ ወደ አዲስ አበባ የሄዱት ከጂቡቲ በመጣ በእራሳቸው አውሮፕላን ከዚያም ወደ ቤተ ጊዮረጊስ በሄሊኮፍተር መሆኑን የቅርብ ምንጭ ለቢቢሲ አሳውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም በተለየ አውሮፕላን እንደሄዱ ይሄው ምንጭ በተጨማሪ ገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ጥበቃ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ከፈረንሳይ መንግሥት በጥቅምት ወር እንዳገኙ የሚታወስ ነው።

የ Facebook ይዘትን ይለፉት

የሚፈልጉት ይዘት የለም

በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.

የ Facebook ይዘት መጨረሻ

የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የሚያተኩርና አብሮ የመሥራት መንፈስን ለማጠናከር የታሰበ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በትዊተር ገፁ እንዲሁም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ድረ-ገፅ ያትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በወርሃ ጥቅምት 8፤ 2011 ፈረንሳይን በጎበኙበት ወቅት አብሮ ለመሥራት የነበራቸውን ፍላጎትም አንፀባርቀው ነበር።

ፕሬዚዳንት ማክሮና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, OFFICE OF THE PRIME MINISTER

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የላሊበላ ቅርስ የሚጠገንበትን ድጋፍ ጠይቀው ከፈረንሳይ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ በማግኘታቸው ነው ፕሬዚዳንት ማክሮ በኢትዮጵያ ላሊበላ የተገኙት።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ለበቢሲ እንደገለፁት የፕሬዚዳንት ማክሮ በላሊበላ መገኘት በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከሩም በተጨማሪ የላሊበላን የጥገናና የማደስ ሥራ ላይ እንዲተባበሩ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

ለፕሬዚዳንቱ በላሊበላ አየር ማረፊያ የአቀባበል ስነ ሥርዓት የተደረገላቸው መሆኑን የገለፁት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ እንዲህ ዓይነት ዝግጅት በላሊበላ ከተማ ሲደረግ የመጀመሪያው ቢሆንም "የላሊበላ ከተማ በታሪክ ዲፕሎማቲክ ከተማ ነበረች" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውሮፓ በነበራቸው ጉብኝት ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በምጣኔ ኃብት ማሻሻያ፣ በወታደራዊ፣ በቅርስ ጥበቃ ዘርፎች ዙሪያ የተለያዩ ስምምነቶችም እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።

ፕሬዚዳንቱ ከርዕሰ ብሔሯ ወ/ሮ ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ ጋር ውይይት ለማድረግ እቅድ ይዘዋል።