ጣልያን በተሸነፈችበት አድዋ ቆንስላዋን ለምን ከፈተች?

የአውሮፓ ሀገራት በጀርመኑ መሪ ቢስማርክ አስተባባሪነት የአፍሪካን ሀገራት ለመቀራመት መስማማታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ሀገራትን በቁጥጥራቸው አዋሉ።

የሀገራቱ መንግሥታት በተስማሙበት መሰረት አፍሪካን በቅኝ ግዛት ቁጥጥር ስር የማዋል ተግባሩ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ቀኝ ገዢ እንድትሆን የተመረጠችው ጣልያንም ጦርዋን አዝምታ ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር በአድዋ ውጊያ ገጥማ ድል ተነሳች።

ጣልያን ከዛ በፊትም በዶጋሊ ሽንፈት አጋጥሟት የነበረ ቢሆንም ይህኛው ሽንፈት ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ የጣልያን ብሄራዊ ክብር ዝቅ ያደረገ ውጊያ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።

ጣልያን በተሸነፈችበት ቦታ ቆንስላዋንለምን ከፈተች?

ጣልያን በአድዋ ጦርነት ከተሸነፈች ከስድስት ወራት በኋላ እዛው ድባቅ በተመታችበት ስፍራ ቆንስላዋን ከፈተች።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ሆና ሳለ ጣልያን ቆንስላዋን በአድዋ መክፈት የፈለገችበት ምክንያት ብዙዎችን በወቅቱ አስገርሟል።

እንዲሁ ሲታይ ጣልያን ቆንስላዋን በአድዋ መክፈት የፈለገችው ሁለቱም ነጻ ሀገራት እንደመሆናቸው መጠን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኘነታቸው እንዲጠናከር ከመፈለግ የተነሳ እንደሆነ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የአርኪኦሎጂ እና ታሪክ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ተክለብርሃን ለገሰ የታሪክ መጽሃፍትን ዋቢ በማድረግ ቢናገሩም የሚቃረን ጉዳይ እንዳለ አልካዱም።

"እነዚህ የተጠቀሱት ምክንያቶች ቆንስላዋን ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በማድረግ ሊሰሩ ይችሉ የነበሩ ናቸው" ይላሉ

ከዚህ ሁሉ በላይ ዋነኛው ምክንያቷ የሚሉት ግን በአድዋ ያጣችውን ድል ለማግኘት ጥናት ለማካሄድ ነበር ይላሉ።

በዚህም መሰረት የጣልያን መንግሥት በአድዋ ጦርነት ላይ ሰራዊቱ ሊሸነፍ የቻለው የተካሄደበትን የአድዋ ገጸ ምድር አስፈላጊውን ጥናት ባለማካሄዱ እንደሆነ ገምግመዋል የሚሉት መምህር ተክለብርሃን ጣልያን ለሽንፈቴ ምክንያት ያለችውንም የአድዋን ተራሮች በቅርበት ለማጥናት ታስቦ ቆንስላዉን እንደተከፈተ ያብራራሉ።

ጣልያን ከ 40 አመታት በኋላ እንደገና ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ቆንስላው የተለያዩ ጥናቶችን በማጥናት ድልን ለመቀዳጀት እንደጠቀማቸውም መምህሩ ያስረዳሉ።

በቆንስላው ቅጥር ግቢ ውስጥ በአድዋ አቅራብያ የሚገኘውን ትልቁን የሰሎዳ ተራራን ያክላል የተባለውን የሰንደቅ አላማ መስቀያ ብረት ይገኛል።

ይህ ትልቅ የሰንደቅ አላማ ብረት የተተከለበት ዋነኛ አላማ ደግሞ ጣልያን በተሸነፈበችበት ቦታ ላይ ሰንደቅ አላማቸውን በረዥም ብረት ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ሽንፈታቸውን ለማካካስ እንደ ምልክትነት እንደተጠቀሙበት በትግራይ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ባለሙያ አቶ ጽጌ ኃይለማርያም ገልጸዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ቆንስላው ከተራሮቹ ጥናት በተጨማሪ የህዝቡን የአሸናፊነት ምስጢርም ለማወቅ እንደነበር የከተማዋ ሽማግሌዎችን በማጣቀስ ይገልፃሉ።

ቆንስላው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ቆንስላው በያኔ የሮማውያን ኪነ ህንጻ ጥበብ የተሰራ ባለ ሶስት ፎቅ ህንጻ ነው። እስካሁን በጣልያንም ይሁን በኢትዮጵያ መንግሥት ምንም እድሳት ያልተደረገለት ሲሆን የትምህርት ቁሳቁሶች ማከማቻ ሆኖ ይገኛል። በውስጡ የወዳደቁ እና የተሰባበሩ ወንበሮች ይገኛሉ።

የትግራይ ባህል እና ቱሪዝም ይህንን ታሪካዊ ቦታ ያውቀው እንደሆነ ለቢሮው ሰራተኛ አቶ ጽጌ ኃይለማርያም ቢቢሲ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን፤ የትግራይ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ለአድዋ ማዘጋጃ ቤት ጥያቄ እንዳቀረበ እና ታድሶ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ሀሳብ እንዳለ ገልፀዋል።

ይህ በኪነ ህንጻው ውብ የሆነውን ቆንስላ በማደስ የጣልያን ጎብኚዎችን ብቻ ትኩረት አድርጎ እንኳ ቢሰራ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ሊሆን እንደሚችል የአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ ተክለብርሃን ያስረዳሉ።