ኔፓላዊቷ ለወር አበባ በተገለለ ጎጆ ሕይወቷ አለፈ የሚሉና ሌሎችም

ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ

• የቀድሞ ሦስት የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ክስ መመስረቱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ክሱ የተመሰረተባቸው ለሁለት ስኳር ፋብሪካዎች የውሃ መርጫ መሳሪያ ሳያስፈልግ በራሳቸው ፍቃድ እንዲገዛ በማድረግ ከ15 ሚሊየን ብር እንዲባክን አድርገዋል በሚል ነው።

ሶማሊያ

• በሶማሊያ የማልትስ ወደብ ሥራ አስኪያጅ መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታወቁ።

'ዲፒ ወርልድ' በተሰኘ የግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ የነበሩት ፓል አንቶኒ ፎርማሶ በቦሳሶ ወደብ አቅራቢያ የተገደሉ ሲሆን አል ሻባብ ጥቃቱን የፈፀምኩት እኔ ነኝ ብሏል።

በተያያዘ ዜና በሞቃዲሾ የገበያ ማዕከል በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ቢያንስ 9 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።

ናይጀሪያ

• የናይጀሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት የሚ ኦሲባንጆ ከሄሊኮፕተር አደጋ መትረፋቸውን ገለፁ።

ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ለሚካሄደው ምርጫ ለቅስቀሳ በማምራት ላይ ሳሉ ነበር ካምባ ላይ አደጋው ያጋጠማቸው።

ለአጠቃላይ የሄሊፕተሩ ሰራተኞችም አደጋውን ለመቆጣጠር ላደረጉት ጥረት በትዊተር ገፃቸው ምስጋና ችረዋል።።

ኔፓል

• የ21 ዓመቷ ኔፓላዊ ለወር አበባ በተገለለ ጎጆ ሕይወቷ ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

አማቷ ሊያይዋት በሄዱበት ወቅት ነበር ለመሞቅ ብላ ባነነደደችው እሳት ጭስ ታፍና ሕይወቷ አልፎ ያገኟት።

በኔፓል ሴት ልጅ የወር አበባዋን አይታ እስከምትጨርስ ተነጥላ እንድትቆይ የሚያደርግ ልማድ ቢኖርም በህግ ከተከለከለ ሰነባብቷል።

ጀርመን

• በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረ ጀርመን ሰራሽ የእጅ ቦምብ በድንች መሃል መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ።

ድንቹ ከፈረንሳይ ወደ ሆንግ ኮንግ የችፕስ ፋብሪካ የተላከ ሲሆን በባለሙያዎች እንዲመክን ተደርጓል።

ቦምቡ ድንች ለማውጣት በተደረገ ቁፋሮ የተገኘ ሳይሆን እንዳልቀረ ተነግሯል።

ጣሊያን

• የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝት እያደረጉ ነው።

ፖፕ ፍራንሲስ 120 000 ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ ላይ የሚካፈሉ ሲሆን ጉዟቸውን ከማድረጋቸው

አስቀድሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እጇ ባለበት የየመን ጦርነት ላይ ትኩረት ሰጥተው ንግግር አድርገው ነበር።

እንግሊዝ

• የ28 ዓመቱ እግር ኳስ ተጨዋች አርጀንቲናዊው ኤሚሊያኖ ሳላና ሌላ አንድ ሰው ጭና ደብዛዋ የጠፋው ትንሿ አውሮፕላን መገኘቷ ተሰማ።

አውሮፕላኗ በእንግሊዝ በሚገኙ 'ቻነል' ደሴቶች የባህር ግርጌ መታየቷን ፍለጋውን የሚመሩት ዴቪድ ሚርስ አስታውቀዋል።

ሕንድ

• በአሜሪካ 129 የህንድ ተማሪዎች መታሰራቸዉን ተከትሎ ደልሒ በሚገኘዉ የአሜሪካ ኤምባሲ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተካሔደ።

ባለፈዉ ረቡዕ የአሜሪካ መንግስት ህጋዊ ካልሆነ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ አገኘኋቸዉ ያላቸዉን 129 ሕንዳዉያን ተማሪዎችን አስሯል።

አሜሪካ

• አሜሪካ ተጨማሪ 2000 ወታደሮችን ወደ ሜክሲኮ ድንበር ልትልክ መሆኑን የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር አስታወቀ።

ቁጥሩ በደቡብ ድንበር አካበቢ ያለውን የወታደሮቿን ቁጥር 4 300 የሚያደርሰው ሲሆን ህገ ወጥ ስደትን ለማስቆም ይረዳል ተብሏል።

***

• በኒውዮርክ እስረኛ ወዳጆቻቸውን ሊጠይቁ የመጡ ግለሰቦች ኤሌክትሪክ መቋረጡን ተከትሎ በእስር ቤቱ በመታገታቸው ተቃውሞ አስነስቷል።

በብሩክሊን የሚገኘው የፌደራል እስር ቤት አካል የሆነው ሜትሮፖሊታን እስር ቤት ውጭ ላይ " ሙቀት የለም፣ መብራት የለም?" የሚሉ መፈክሮችን በመያዝ ድምፃቸውን ያሰሙ እንደነበር ተዘግቧል።