ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ #10YearChallenge አስደንጋጭ እውነታዎች፤ ካልተቀየሩት የዓለማችን እውነታዎች ዋና ዋናዎቹ
የዛሬ አሥር ዓመት የት ነበሩ? እ.አ.አ በ2009 ማይክል ጃክሰን ከዚህች ዓለም በሞት የተለየበትና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሥልጣን የተረከቡት ዓመት ነበር።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የማህበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ከአሥር ዓመታት በፊት የተነሱትን ፎቶግራፍ ከቅርብ ጊዜ ፎቶግራፍ አጠገብ አድርገው '10YearChallenge' ከሚል ሃሽታግ (የመሰላል ምልክት) ጋር ሲያጋሩ ከርመዋል።
በጣም አረጀሁ የሚለውን ስሜት ትተን መለስ ብለን የዓለማችንን ለውጦች ስንመለከት ግን ምንም ያለተቀየሩ ነገሮች ጎላ ይላሉ።
እስከዛሬ ያሉት
ለአሥር ዓመታት ኮማ ውስጥ የነበረ ሰው ቢነቃ የዓለማችን ብዙ መሪዎች ሳይቀየሩ ይደርስባቸዋል።
ከእነዚህ መካከል የመንግሥት ግልበጣ ሙከራዎች ያልበገሯቸው፣ ህገመንግስት የፃፉና በተደጋጋሚ ምርጫ ያሸነፉ መሪዎች ከአሥር ዓመት በፊት በነበሩበት እስካሁን አሉ። የዓለም ፖለቲካ ብዙ ለውጦችን ቢያስተናግድም እነርሱ ግን እስካሁን ሥልጣን ሳይለቁ የቀሩ ናቸው።
በአንፃሩ ደግሞ ስዊዘርላንድ ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ አሥር የተለያዩ ፕሬዚዳንቶች ነበሯት። ይህም የሆነው በስዊዘርላንድ ህገመንግስት መሠረት የፕሬዚዳንት ጊዜ ገደብ በአንድ ዓመት የተወሰነ በመሆኑ ነው።
እስከዛሬ ይቀልጣል
በአኗኗራችን ምክንያት እየቀለጡ ስላሉት የበረዶ ክምሮች ለረጅም ዓመታት ስንሰማ ቆይተናል። አመለካከታችን ግን ምንም ያህል አልተቀየረም።
የአየር ንብረት መለዋወጥ በመጀመሪያ አቅማቸው ደካማ የሆኑትን ሃገራት በከባዱ እንደሚያናጋ አይካድም፤ ሆኖም ግን የዚህን ተጽዕኖ እንዲቀንስ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንኳን ለመድረስ የዓለም መሪዎችን 21 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል።
በፈረንጆቹ 2018 የመጨረሻ ወር በፖላንድ የተፈረመው 'COP24' የተሰኘው ስምምነት በዚህ ረገድ የመጀሪያው መመሪያ ሲሆን እሱም የጎጂ ጋዞች ልቀትን ለመቀነስ እንዲሠራ መንግሥታትን ይጠይቃል።
በሌላ በኩል ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ምንም ለውጥ አልታየም፤ የምድርም ሙቀት እየጨመረ ነው የመጣው።
በ2009 በተደረገው የናሳ ውጤት መሠረት ከ1951 እስከ 1980 ከነበረው የምድር አማካይ የሙቀት መጠን 0.63 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበረ ሲሆን በ2017 ግን 0.90 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሷል።
እስካሁን ድህነት
የተቀየረ ነገር ቢኖር ከአሥር ዓመት በፊት ነዳጅና ባንክ ይመሩ የነበሩት ሃብታም ድርጅቶት ብቻ ነበሩ።
ፋይናሻል ታይመስ ግሎባል 500 የተሰኘው ጥናት ዓመታዊ የዓለምን 500 ትልልቅ ድርጅቶች የሚያነፃፅር ሲሆን በ2018 ከወትሮው በተለየ መልኩ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የንግዱን ዓለም እንደተቀላቀሉ አሳውቋል።
ያለተቀየረ ነገር ቢኖር ግን በሃብታሞችና አቅማቸው ደካማ በሆኑት መካከል ያለው ክፍተት ነው። እንደውም ከ2008 የዓለም የገንዘብ ነውጥ በኋላ ክፍተቱ እየጨመረ መጥቷል።
በእንግሊዝ ፓርላማ በተደረገው ጥናት መሠረት ከ2008 እስከ 2017 በነበረው ጊዜ ውስጥ 1% የሚሆኑት የዓለም ሃብታሞች ሃብት በ6% ያደገ ሲሆን 99% የሚሆኑት የዓለም አቅመ ደካማዎች ደግሞ ሃብታቸው በ3% ብቻ ነው የጨመረው።
ጥናቱ አክሎም 1% የሚሆኑት የዓለም ሃብታሞች በ2030 የዓለምን 64% ሃብት ይይዛሉ በማለት ተንብይዋል።
እስካሁን የእኩልነት ጉድለት
ሴቶችን ስለማጎልበትና መብታቸውን ስለማስከበር ብዙ ቢወራም የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ግን ምንም ያህል አልተቀየረም።
በርግጥ አንዳንድ ነገሮች ተቀይረዋል ለምሳሌ በእንግሊዝ ከሴት ቀሚስ ሥር ፎቶግራፍ ማንሳት በሕግ የሚያስቀጣና ለእስር የሚዳርግ ሆኗል። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በተደበቁ ካሜራዎች የተቀረጹ እርቃናቸውን ያሉ ሴቶችን የሚሳየውን ትልቁን ድረ-ገፅ አስዘግቷል።
በሳዑዲ አረብያ ደግሞ ሴቶች በስቴድየም ገብተው የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ማየት ከመፍቀዱም ባሻገር አንዳንድ ሴቶች መንጃ ፈቃድ ማውጣትም ችለዋል። በሕንድ ደግሞ ሴቶች ከዚህ ቀደም ተከልክለው የነበሩበትን የአምልኮ ቦታዎች ከወንዶች እኩል መግባት ተፈቅዶላቸዋል።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ በኔፓል ሴት ልጅ የወር አባባዋ ላይ ስትሆን እንድትቀመጥ በሚደረግበት ጎጆ ውስጥ ብዙዎች ይሞታሉ። በአንዳንድ አፍሪካ ሃገራት ደግሞ በግርዛት ምክንያት ሴቶች ህይወታቸውን ያጣሉ።
የእኩልነት ጉዳይ በዓለም ላይ ዝግ ባለ ፍጥነት እየተሻሻለ ይገኛል። ባለፈው ዓመት በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የደምወዝ ልዩነት ብቻ እኩል ለማድረግ 202 ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ተነግሯል።
በሥልጣን እስካሁን የቆዩት ስም ዝርዝር:
የመጀመሪያ ረድፍ ከግራ ወደ ቀኝ : ቴዮዶሮ ኦብያንግ ምባሶጎ (ኢኳቶሪያል ጊኒ)፣ ኤሞማሊ ራህሞን (ታጂኪስታን)፣ ኢሳያስ አፈወርቂ (ኤርትራ)፣ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ (ቤላሩስ)፣ ፋኦሬ ኛሲንቤ (ቶጎ)፣ አንጌላ ሜርኬል (ጀርመን)፣ ኢልሃም አሊዬቭ (አዘርባይጃን)፣ ፒዬር ንኩሩንዚዛ (ቡሩንዲ)፣ ኤቮ ሞራሌስ (ቦሊቭያ)
ሁለተኛ ረድፍ ከግራ ወደ ቀኝ : ፖል ቢያ (ካሜሩን)፣ ጆሴፍ ካቢላ (ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ)፣ ቤንጃሚን ኔታንያሁ (እስራኤል)፣ ማሕሙድ አባስ (ፓሌስታይን)፣ ኑርሱልታን ናዛርባዬቭ (ካዛክስታን) ፣ አብደላዚዝ ቦኡትፍሊካ (አልጄሪያ) ፖል ካጋሜ (ሩዋንዳ) ዮዌሪ ሙሴቬኒ (ዩጋንዳ) ኦማር አል-ባሺር (ሱዳን)
የመጨረሻ ረድፍ ከግራ ወደ ቀኝ : አሊ ቦንጎ ኦዲንባ (ጋቦን)፣ ኢድሪስ ዴቢ (ቻድ)፣ ቭላድሚር ፑቲን (ሩስያ)፣ ዴኒስ ሳሱ ንጌሱ (ኮንጎ)፣ ሬሴፕ ታዪፕ ኤርዶጋን (ቱርክ) ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ (ጂቡቲ) ባሻር አል-አሳድ (ሶሪያ) ጉርባንጉሊ ቤርዲሙሃሜዶ (ቱርክሜኒስታን)