ከተሜነትና የሙቀት መጨመር የተመቻቸው አይጦች ስጋት ሆነዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ ዋና ከተማ ነዋሪዎች ከሁለት ዓመት በኋላ የከንቲባ ምርጫ ያካሂዳሉ፤ በዚያ ጊዜ ለሚካሄደው ምርጫ አሁን በከንቲባነቱ መንበር ላይ የሚገኙት ግለሰብ በድጋሚ እንዳይወዳደሩ ከሚያደርጓቸው የከተማዋ ችግሮች መካከል የአይጦች መብዛት ይጠቀሳል።
በናይጄሪያም በቅርቡ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በአይጦች በመወረሩ ፕሬዝዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ለበርካታ ሳምንታት ከቤታቸው ሆነው ነበር ሥራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት።
ስፖርትና ሙዚቃን ጨምሮ በበርካታ ነገሮች ትታወቅ የነበረችው የችካጎ ከተማ አሁን የአሜሪካ "የአይጦች መዲና" የሚል ስያሜም ተጨምሮላታል።
ኢንዶኔዢያ በየዓመቱ ከምትሰበስበው የሩዝ ምርት ውስጥ 17 በመቶው በአይጦች ምክንያት እንደሚወድምባት ሪፖርት አድርጋለች።
በአይጦች ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ስንመለከትና እንደጦርነት ብናየው የሰው ልጅ እየተሸነፈ ነው ማለት እንችላለን። ወደፊትም ችግሩ እየከፋ ሊሄድ እንደሚችልም ይገመታል።
ሳይንቲስቶች እንደሚሉት የከተሞች መስፋፋትና የዓለም ሙቀት መጨመር የአይጦችን ቁጥር ከፍ ስለሚያደርገው፤ በሰዎች ዙሪያ የሚገኙት አይጦች ተራ ችግሮች ሆነው አይቀጥሉም።
በፍጥነት መራባት
አይጦች ለበሽታ መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ፣ የምግብ ዋስትናን ለአደጋ ያጋልጣሉ እንዲሁም በግንባታዎች ላይም ችግርን ያስከትላሉ። በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በአይጦች ሳቢያ በየዓመቱ አሜሪካ ውስጥ 19 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ውድመት ይደርሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት እንደሚያመለክተው ከ30 ዓመት በኋላ አሁን ያለው 55 በመቶ የሚደርሰው የምድራችን የከተማ ነዋሪ ሕዝብ አሃዝ ወደ 70 በመቶ ከፍ ይላል።
ብዙ ሰው በከተሞች ሲኖር በርካታ ህንፃዎች ይኖራሉ በዚህም በሰዎች አቅራቢያ እየኖሩ ፍርፋሪ በመለቃቀም ለዘመናት የኖሩት አይጦች ተጨማሪ ምግብና መጠለያን ያገኛሉ ማለት ነው።
ከአይጥ ዝርያዎች መካከል ራተስ ኖርቬጂከስ ተብሎ የሚታወቀው ቡናማ የአይጥ ዝርያ በምድር ላይ በየቦታው በስፋት የሚገኝ ዋነኛው ችግር ፈጣሪ ነው።
ከፍተኛ የሙቀት መጠን በአይጦች መካከል ያለውን የመራባት ዑደትን ያራዝመዋል። ባለሙያዎች እንደሚሉት ጥንድ አይጦች አመቺ ሁኔታን ካገኙ በአንድ ዓመት ውስጥ 1250 አባላት ያሉት ቤተሰብ ሊፈጥሩ ይችላሉ።
''አይጦች የማይበገሩ ጠላቶቻችን ናቸው ልናጠፋቸው እንደማንችል መረዳት ያስፈልገናል። የቀሩት በፍጥነት መራባት ስለሚችሉ መግደል መፍትሄ አይሆንም" ይላሉ የለንደኑ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ስቲቭ ቤልሜይን።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጦርነት ከአይጦች ጋር
"ከአይጦች ጋር የገጠምነው ጦርነት ያልተሳካበት ምክንያት ከእነሱ ቀድሞ በማቀድና በመዘጋጀት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአነሱን ጥቃት እየተከተልን በመንቀሳቀሳችን ነው" የሚሉት በኒው ዮርኩ ፎርድሃም ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ፓርሰንስ ናቸው።
ጨምረውም አይጦችን በተመለከተ ያለው ዕውቀት በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ። "በሚያስደነግጥ ሁኔታ አይጦችን በተመለከተ የተደረጉ ጥናቶች ውሱንነት አለ" ይላሉ።
ባለሙያዎች እንደገመቱት በዓለማችን ላይ ባለፉት አንድ ሺህ ዓመታት ውስጥ በተከሰቱ በሁሉም ጦርነቶች ምክንያት ከሞቱት ሰዎች የበለጠ ቁጥር ያላቸው በአይጦች ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።
አይጦች በ14ኛው ክፍለ ዘመን ተከስቶ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን የአውሮፓን ህዝብ የፈጀው የጥቁር ሞት ወረርሽኝ ምክንያት እንደሆኑ ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት አይጦችን ለማጥፋት በአብዛኛው እንደ መፍትሄ የሚወሰደው በመርዝ መግደል ነው። ነገር ግን ይህ መንገድ ሰዎችንና ሌሎች እንስሳትን ከመጉዳት በተጨማሪ በምንኖርበት አካባቢ ላይ አደጋን ያስከትላል።
አጥኚዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንደደረሱበት አይጦችን እነሱን ለመግደል ጥቅም ላይ የሚውሉ አንዳንድ መርዞች የመላመድ ባህሪን እያመጡ ነው። በተጨማሪም በመርዝ አይጦችን መግደል እየተወገዘ ያለ ድርጊት ሆኗል።
ድመቶችም መፍትሄ አልሆኑም
የአይጦችን ወረራ ለመከላከልና ለማጥፋት አንዳንድ ከተሞች አዳኝ ድመቶችን እስከማሰማራት ደርሰዋል። ለምሳሌም የዋሽንግተን ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለቤት አልባ ድመቶችን አሰማርታለች።
ቢሆንም ግን አይጦችን ለማሳደድ የተሰማሩት ድመቶች የተፈለገውን ያህል ውጤት እንዳላስገኙ በጥናት ተረጋግጧል። 150 አይጦች ይኖሩበታል በተባለ አንድ ስፍራ በተሰማሩ ድመቶችና አይጦች ላይ ለአምስት ወራት በተደረገ ጥናት 78 ጊዜ ፊት ለፊት የመፋጠጥ አጋጣሚዎች በፈጠርም ድመቶቹ ሦስት ጊዜ ለማጥቃት ሞክረው ሁለቱን ብቻ መግደል ችለዋል።
"ድመቶችና አይጦች ፊት ለፊት በሚገናኙበት ጊዜ በተለይ ደግሞ አይጦች መጠናቸው ከፍ ካለ፤ አይቶ እንዳላየ ይተላለፋሉ አሊያ ደግሞ እራሳቸውን ከፍጥጫው ያርቃሉ'' ሲሉ የፃፉት በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩት ግሪጎሪ ግላስ ናቸው።
አይጦችን ማምከን
ባለፈው ዓመት ሴንሴቴክ የተባለው የአሜሪካ ተቋም ዓለምን ይቀይራል ያለውን ሴት አይጦችን የሚያመክን መድሃኒት መፍጠሩን ይፋ አድርጓል። በተለያዩ ቦታዎች ጥቅም ላይ ውሎ በውጤቱም የአይጥ መርዝ ከመጠቀም አንፃር 46 በመቶ የአይጦችን መጠን ለመቀነስ እንዳስቻለ ድርጅቱ ተናግሯል።
ይህ ዘዴም ከሁለት ሚሊዮን በላይ አይጦች ይገኙባታል ተብሎ በሚታመንባት በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ባለፈው ዓመት ተሞክሯል። ነገር ግን አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት ዘዴው ችግሩን የሚያስወግድ ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
"ምግብ ለማግኘት የሚኖረው ሽሚያ ስለሚቀንስ፤ የሚያመክነውን መድሃኒት ያልወሰዱ አይጦች የበለጠ የመራባት እድላቸው ሰፊ ይሆናል" በማለት ለኒው ሳይንቲስት መጽሔት ስጋታቸውን የተናገሩት የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያ የሆኑት ፒተር ባንክስ ናቸው።
አይጦችን ለመቆጣጠር ካሉት አማራጮች መካከል ባለሙያዎቹ የሚያስማማው የአይጦችን የምግብ አቅርቦት ማቋረጥ ቁጥራቸውን ለመቀነስ ቁልፍ ዘዴ እንደሆነ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አይጦችና ምግብ
"ባለስልጣናት በከተሞች ውስጥ ያለውን የቆሻሻ ማጠራቀሚያና የተበላሸ የንጽህና ሁኔታን ማስተካከል ከቻሉ አይጦችን በመቆጣጠር በኩል መሰረታዊ ለውጥን ያመጣል" ይላሉ ስቴቨን ቤልሜይን።
ስለዚህም አይጦች የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው "እርስ በርስ ይበላላሉ" የሚሉት ደግሞ ማይክ ፓርሰንስ ናቸው።
"አይጥ መርዝን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ንግድ ያንቀሳቅሉ። ነገር ግን ቆሻሻችንን በአግባቡ ማስወገድ ከተቻለ አይጦችን በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል።
"የምግብ ዕጥረት ሲከሰት አይጦች ቁጥር ከሚያገኙት ምግብ ጋር ተመጣታኝ ይሆናል። ይህም ማለት የመራባት መጠናቸው ይቀንሳል እርስ በርስ መጣላት ይጀምራሉ።"
"የሰው ልጅ በዓለም ዙሪያ እንዲስፋፉ ካደረጋቸው ፍጥረታት መካከል አይጦች ጥሩ ምሳሌ ናቸው። እነሱም በደረሱበት አዳዲስ ቦታዎች ሁሉ በቀላሉ ተላምደው በመኖር በኩል የተሳካላቸው ሆነዋል" ይላሉ የሌስተር ዩኒቨርሲቲው ባለሙያ ጃን ዛላሲዊችዝ።
ጨምረውም "አይጦች በምድራችን መጪ ዘመን ዋነኛ ሚና ካላቸው ፍጥረታት መካከል የሚመደቡ ሲሆኑ ምናልባትም የሰው ልጅ የምድር ላይ ህላዌ ካበቃ እነሱ ግን ሊቀጥሉ ይችላሉ" ይላሉ።












