ደቡብ አፍሪካ ሚኒስትሯ ሊንድዌ ሲሱሉ ሴተኛ አዳሪ ተብላ በሩዋንዳ ጋዜጣ መሰደቧን ተቃወመች

ሊንድዌ ሲሱሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሩዋንዳ የሚገኝ አንድ የመንግሥት ደጋፊ ጋዜጣ አንዲት ሴት የደቡብ አፍሪካ ሚኒስትርን "ሴተኛ አዳሪ" ብሎ በመጥራቱ በምላሹ ደቡብ አፍሪካ በፕሪቶሪያ የሚገኘውን የሩዋንዳ ልዩ መልዕከተኛ አስጠርታለች።

ይህንን ዘለፋ ያስተናገዱት የውጭ ኃገራት ሚኒስትር የሆኑት ሊንድዌ ሲሱሉ ሲሆኑ፤ ከፍተኛ ኃላፊነት ያላቸው የሩዋንዳ ባለስልጣንም በትዊተር ገፃቸው ተችተዋቸዋል።

የሚኒስትሯ ቃል አቀባይ ዘለፋው ተቀባይነት እንደሌለውና ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሊንድዌ ሲሱሉ በቅርቡ በግዞት ላይ ካሉት ሩዋንዳዊ ፖለቲከኛ ጋር መገናኘታቸው በሁለቱ ኃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ጥላሸት እንደቀባው ተዘግቧል።

በባለፈው ወር በነበረውም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሩዋንዳን የቀድሞ የጦር ጄነራል ፋውስቲን ካዩምባ ንያምዋሳ በጆሐንስበርግ ማግኘታቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ የተቃዋሚ ፓርቲ የመሰረቱት ንያምዋሳ ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ድርድር ለመጀመር ማሰባቸው "እንዳስደነቃቸውም" ተናግረዋል።

ፋውስቲን ካዩምባ ንያምዋሳ ከፕሬዚዳንት ፓውል ካጋሜ ጋር ከተጣሉ በኋላ ከአውሮፓውያኑ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በግዞት መኖር መጀመራቸው ተዘግቧል።

ከጋዜጣው ዘለፋ በተጨማሪ የሩዋንዳ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቨር ንዱንጊርሔ በትዊተር ገፃቸው ደቡብ አፍሪካን ተችተዋል።

በፅሁፋቸውም እንዳተቱትም "ማንኛውም ደቡብ አፍሪካዊ ኃገርን ለመበጥበጥ ከሚሞክርና ከተከሰሰ ወንጀለኛ ጋር ግንኙነት መፍጠር ይችላሉ ነገር ግን በሂደቱ ውስጥ ሩዋንዳን ማሳተፍ አይችሉም።" ብለዋል።

የሩዋንዳ መንግሥት ደጋፊ ጋዜጣም ሚኒስትሯን የፋውስቲን ካዩምባ ንያምዋሳ "ሴተኛ አዳሪ" በሚል ርዕስ መሳደቡን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ምንጭ በጆሀንስበርግ ለቢቢሲ ዘጋቢው ሚልተን ንኮሲ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ፅሁፉ ከጋዜጣው ቢወገድም አደጋው ማድረሱን ግን ጋዜጠኛው ጨምሮ ዘግቧል።

የሚኒስትሯ ቃል አቀባይ ንድሁዎ ማባያ በበኩላቸው ፕሪቶሪያ ለሚገኘው የሩዋንዳ መንግሥት መልዕክተኛ የጋዜጣው ዘለፋ በምንም መንገድ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

ከአራት አመታት በፊት ጆሐንስበርግ በሚገኘው ቤታቸው ላይ ጥቃት የደረሰባቸው ፋውስቲን ካዩምባ ንያምዋሳ ጋር በተያያዘ ሶስት ዲፕሎማቶችን ደቡብ አፍሪካ አባራ ነበር።

በምላሹም ሩዋንዳ ስድስት የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማቶችን አባረረች።

ፖለቲከኛው በዚሁ ግዞት ላይ ባሉበት ወቅት ብቻ ከሁለት የግድያ ሙከራዎች ተርፈዋል።

በአንደኛው ጥቃትም አራት የታጠቁ ሰዎች ፖለቲከኛው ሆድ ላይ በጥይት በማቁሰል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

በሁለቱ ኃገራት መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረው የቀድሞው የሩዋንዳ የደህንነት ኃላፊ ኮሎኔል ፓትሪክ ካሬጋያ ከአራት ዓመታት በፊት በሆቴል ውስጥ ተገድለው በመገኘታቸው ነው።

ከተገደሉ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ፕሬዚዳንት ካጋሜ " ሩዋንዳን ከድቶ ተመጣጣኝ ቅጣት አለመቀበል አይቻልም። ሌሎችም በህይወት ያሉት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የዘሩትን ይለቅማሉ" ብለዋል።