አሜሪካ ውስጥ ለየት ያለ ደም ላላት ህፃን ለጋሽ ለማግኘት ዘመቻ ተጀመረ

ህፃኗ ዘይነብ ሙጋል

የፎቶው ባለመብት, DIVULGAÇÃO/ONEBLOOD

የምስሉ መግለጫ, ዘይነብ ሙጋል

በካንሰር ህመም እየተሰቃየች ያለችው የሁለት ዓመት ህፃን በሽታውን ለመግታት የሚያስፈልጋትን በርካት ያለ መጠን ያለውን የተለየ የደም ዓይነት ከለጋሾች ለማግኘት ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተጀመረ።

አሜሪካ ፍሎሪዳ ውስጥ ያለችው ህፃኗ ዘይነብ ሙጋል በዓለም ላይ ለየት ያለ የደም ዓይነት ካላቸው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዷ ናት። ይህም የሚያስፈልጋትን የደም አይነት የሚለግሳት ሰው ለማግኘት አስቸጋሪ አድርጎታል።

እስካሁን አንድ ሺህ የሚደርሱ የደም ናሙናዎች ቀርበው ቢመረመሩም ከእሷ ደም ጋር ተዛማጅ ሆነው የተገኙት ሦስቱ ብቻ ናቸው። ሃኪሞች እንደሚሉት ለህፃኗ 10 ተመሳሳይ ደም ያላቸው ለጋሾችን ማግኘት ያስፈልጋል።

ለዘይነብ ደም ለማግኘት ዘመቻውን እየመራ የሚገኘው 'ዋንብለድ' የተሰኘው የበጎ አድራጎት የደም ባንክ የላብራቶሪ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ፍሬዳ ብራይት እንደሚሉት፤ የህፃኗ ደም የተለየ ነው ምክንያቱም በብዙ ሰዎች ደም ውስጥ የሚገኘውና ኢንብ ተብሎ የሚታወቀው አንድ የደም ክፍል የላትም።

ስለዚህም የህፃኗን ህይወት ለመታደግ በተመሳሳይ ይህ አይነቱ የደም ክፍል የሌላቸው ለጋሾችን ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነው። ሌላ አይነት ደም ከተሰጣት ደግሞ ሰውነቷ ፈጽሞ ሊቀበለው አይችልም።

ይህ አይነቱ የደም አይነት ያልተለመደ መሆኑን የሚናገሩት የላብራቶሪው ሥራ አስኪያጅ ብራይት "ከ20 ዓመታት በላይ በዚህ ሙያ ላይ ተሰማርቼ የቆየሁ ቢሆንም እንዲህ አይነቱ ነገር ሲያጋጥመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው" ብለዋል።

ለህፃኗ ደም ለጋሽ ለማግኘት የሚደረገውን ዘመቻ እየመሩ ያሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ለጋሾች ተመሳሳይ የደም አይነት እንዲኖራቸው ከመፈለጉ በተጨማሪ በተለይ የፓኪስታን፣ የሕንድ ወይም የኢራን ዝርያ ያላቸውና የደም አይነታቸው ደግሞ ኦ ወይም ኤ ሊሆን ይገባል።

የሦስቱ ሃገራት ዝርያ ያላቸው ለጋሾች ብቻ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ተፈላጊው የደም ዓይነትን ከነዚህ ሃገራት ውጪ ካሉ ሰዎች የማግኘቱ እድል ከሞላ ጎደል ዜሮ በመሆኑ ነው ተብሏል።

ተመሳሳይ የደም አይነት አላቸው ከሚባሉት ሰዎች መካከልም ከህፃኗ የደም አይነት ጋር የሚዛመድ ደም ያላቸው የሰዎች ቁጥር ከአራት በመቶ ያነሰ ነው።

የዘይነብ አባት እንደተናገሩት ልጃቸው ኒዩሮብላስቶማ ተብሎ የሚታወቀውና በአብዛኛው ህፃናት ልጆች ላይ የሚያጋጥመው የካንሰር አይነት እንዳለባት የታወቀው ባለፈው ጥቅምት ላይ ነበር።

ቤተሰቧ ይህንን አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ ክፉኛ ነበር በሃዘን የተመታው የበለጠ ሃዘናቸውን ያበረታው ደግሞ የዘይነብ ደም ለየት ያለ መሆኑና የሚያስፈልጋትን ደም ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ነበር።

ህፃኗን እያከሙ ያሉት ሃኪሞች እንደሚሉት በኬሞቴራፒ ህክምና የካንሰሩ እጢ መጠን እየቀነሰ ቢሆንም፤ ዘይነብ ተጨማሪ ህክምናና በርከት ያለ ደም ያስፈልጋታል።

"እየተፈለገ ያለው ደም ዘይነብን ከህመሟ ባያድናትም፤ ለካንሰር የሚሰጣትን ህክምና ለመቋቋም ግን እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ ብራይት።