የኦሮሞ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደረሱ

ዳውድ ኢብሳ፣ አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር መረራ ጉዲና

ከ14 በላይ የሚሆኑ የኦሮሞን ጥያቄ ማዕከል ያደረጉ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ስምምነቱ የተደረሰው በዛሬው ዕለት 'የኦሮሚያ ተጨባጭ ሁኔታ እና የዲሞክራሲ ሽግግር'' በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው።

የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በሰጡት መግለጫ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ፎረም እንዲቋቋም ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል።

ፎረሙ በፓርቲዎች መካከል ችግር ሲያጋጥም በመደማመጥ እና በውይይት ለመፍታት እንዲያስችልና ፓርቲዎቹ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አንድ መድረክን ሊፈጥሩ የሚችሉበት ሁኔታም እንዳለ ታምኗል።

የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ በመግለጫው ላይ "የህዝብ ጥያቄን መመለስ የሚቻለው አንድነት ሲኖረን ነው። መንግሥት የህግ የበላይነትን በሚያስከብርበት ጊዜ እኛም የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እንወጣለን" በማለት ቃል ገብተዋል።

የኦፌኮ ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው "አሁን የተመዘገበው ድል በእልህ አስጨራሽ መስዋእትነት የተገኘ በመሆኑ፤ የወጣቱ እና የህዝቡ እንድነት ማጠናከር አለበት" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በውይይቱ ላይ ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ 'የት ደረስን?' በሚል ርዕስ አንድ ንግግር አቅርበዋል። የኦሮሞ ህዝብ ሰላም እና ዲሞክራሲን መፈለጉ ህዝቡ ያለውን ጥንካሬ ማሳያ እንደሆነ ገልፀው ነገር ግን የፖለቲካ ክፍፍል እና የአመራር እጦት በኦሮሞ ፖለቲካው ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶች ፈታኝ ችግሮች እንደሆኑ በንግግራቸው ዳስሰዋል።

ውይይቱን የመሩት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ሀገሪቱ እየሄደችበት ያለውን ለውጥ አድንቀው ''ይህች አገር እንደ አገር ለመቀጠል ትክክለኛው የሽግግር ሰዓት ይህ ነው'' ብለዋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ "የኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ ሴራዎች እየተጠነሰሱ ነው ያሉ ሲሆን ህዝቡም ይህን አይነት ተግባር በንቃት መከታተል አለበት" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።