ዓለማችን "ክትባቱ ቸል በመባሉ ምክንያት" የኩፍኝ ወረርሽኝ ያሰጋታል ሲል አለም አቀፉ ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለም አቀፍ ደረጃ የኩፍኝ ወረርሽኝ እንዳለ የጠቀሰው የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዘገባ ባለፈው አመት ብቻ አንዳንድ ሀገራት "ረዘም ላለና ለከፋ ወረርሽኝ" ተጋልጠው ነበር ብሏል።
የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በሁሉም የአለማችን ሀገራት በ2016 ከታየው በ2017 ሰላሳ በመቶ ጨምሯል።
ባለሙያዎች ለቁጥሩ መጨመር እንደምክንያት ያነሱት ስለ ክትባቱ ያለው የተሳሳተ መረጃንና የህክምና አገልግሎት ስርአቶች መውደቅን ነው።
የኩፍኝ ክትባት የሚሊየኖችን ህይወት ይታደጋል ሲሉም ያስረዳሉ።
ኩፍኝ ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ሁኔታ የሚተላለፍ ሲሆን በወቅቱ ካልታከመም የአይን ብርሃንን እስከማጣት ሊያደርስ፣ ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል እብጠትና ለኢንፌክሽን ያጋልጣል።
የአለም አቀፉ ጤና ድርጅትና የአሜሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በጋራ ያወጡት ጥናት ኩፍኝን ላለፉት 17 ዓመታት ሲከታተሉ እንደነበር ያሳያል።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከ17 ዓመት ወዲህ የኩፍኝ ወረርሽኝ በከፍተኛ መጠን የጨመረ ነው። ይህ የመጀመሪያው አመት ሲሆን 110 ሺህ ከኩፍኝ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሞቶችም ተመዝግበዋል።
ባለሙያዎቹ በዚህ አመትም ያለው እንቅስቃሴ በተመሳሳይ መልኩ መቀጠሉ ያሳሰባቸው ሲሆን ይህም በአውሮጳ የክረምት ወራት ተመሳሳይ የታማሚዎች ቁጥር አእንዲመዘገብ አድርጓል ይላሉ።
ከዚህ በፊት በሽታው ጠፍቶባት የነበረችው ቬንዚዌላ የጤና ስርዓቷ በምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ከወደመ በኋላ ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር ተመዝግቦባታል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገር ሀገር በርካታ ሰዎች መንቀሳቀሳቸው በሽታው በፍጥነት ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ባለፈው ዓመት በዩክሬን፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ግሪስ የኩፍኝ ወረርሽኝ መጨመር ታይቷል።

















