''ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ'' የተባለለትና አሜሪካ በኢራን ላይ የተጣለችው ማዕቀብ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

ኢራናውያን ተቃዋሚዎች በቀድሞ የአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የትራምፕ አስተዳደርን የተቃወሙ ኢራናውያን በቀድሞ የአሜሪካን ኤምባሲ ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል

''ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ'' የተባለለት ማዕቀብ በነዳጅ ሃብቷ በበለጸገችው ኢራን ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

ከሶስት ዓመታት በፊት አሜሪካ እና ኢራን ያደረጉትን የኒውክሌር ስምምነት ተከትሎ ተነስተው የነበሩት ማዕቀቦች እንደገና ተግባራዊ እንዲደረጉ የትራምፕ አስተዳደር እየሠራ ነው።

ይህ የባንክ፣ ነዳጅ እና የመርከብ ትራንስፖርት አገልግሎትን የሚመለከተው ማዕቀብ ኢራን እና የንግድ አጋሮቿ ጭምር ላይ ያነጣጠረ ነው።

በትራምፕ አስተዳደር የተበሳጩ በርካታ ኢራናውያን ''ሞት ለ አሜሪካ'' የሚሉ መፈክሮችን በአደባባይ ሲያሰሙ ነበር።

የኢራን የጦር ኃይልም የሃገሪቱን የመከላከያ ብቃት ለማስመስከር ሰኞና ማክሰኞ አየር ኃይሉ ልምምዶችን ያደርጋል ሲል ተሰምቷል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ''ኢራን ላይ የሚጣለው ማዕቀብ በጣም ጠንካራ ነው። እስካሁን ከጣልናቸው ማዕቀቦች ሁሉ ጠንካራው ነው። ኢራን የምትሆነውን አብረን እናያለን፤ የማረጋግጥላችሁ ግን አካሄዳቸው ጥሩ አይደለም።'' ብለው ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የሳይበር ጥቃቶችን፣ የሚሳዔል ሙከራዎችን እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ሚሊሻዎችን እና የሽብር ቡድኖችን መደገፍ ማቆም አለባት ይላል።

ፕሬዚዳንት ራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Huw Evans picture agency

ይህ በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

ከ70 በላይ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ መርከቦች እና አውሮፕላኖች በማዕቀቡ ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ። ማዕቀቡ የሃገሪቱን ዋነኛ ባንኮች፣ ነዳጅ ላኪ ኩባንያዎች እና የመርከብ ትራንስፖርት ኩባንያዎችን ዒላማ አድርጓል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማዕቀቡን ተከትሎ ራሳቸውን ከኢራን አግልለዋል ብለዋል።

ፖምፔዎ ጨምረው እንደተናገሩት ኢራን የምትልከው የነዳጅ ብዛት በቀን በአንድ ሚሊዮን በርሜል ቀንሷል።

እንግሊዝ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ማዕቀቡን ተቃውመዋል። ሃገራቱ ከኢራን ጋር ህጋዊ ንግድ መፈጸም የሚፈልጉ አውሮጳዊ ኩባንያዎች የአሜሪካ ማዕቀብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው የተለያዩ የክፍያ ስርዓቶችን እንደሚዘረጉ ቃል ገብተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በስም ያልጠቀሳቸው ሰምንት ወዳጅ ሃገራት ከኢራን ነዳጅ እንዲያስገቡ ፈቀዷል። ተንታኞች ከእነዚህ አገራት መካከል ጣሊያን፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቱርክና ጃፓን ይገኙበታል ይላሉ።