የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጥቃት፡ የግብፅ ፖሊስ 19 እስላማዊ ታጣቂዎችን ገደለ

የኮፕቲክ ክርስቲያኖች የሟቾችን አስክሬን ተሸክመው ወደ ቀብር ሲሄዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በክርስቲያኖቹ ላይ የደረሰው ጥቃት በርካቶችን አስቆጥቷል

በግብፅ የኮፕቲክ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት የፈፀሙ 19 እስላማዊ ታጣቂዎች በፖሊስ እንደተገደሉ የግብፅ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚንስትሩ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ታጣቂዎቹ በምዕራብ ሚነያ ግዛት በሚገኝ በረሃ ለማምለጥ ሲሞክሩ በፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት ሊገደሉ ችለዋል።

በወቅቱ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢያግቧቧቸውም ስላልቻሉ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ እንደተገደሉ ሚንስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ሚንስትሩ ይህንኑ ለማረጋገጥ የሟቾቹን አስክሬን ፣ ታጣቂ ቡድኖቹ መሽገውበታል የተባለውን ድንኳንና ፣ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም የቡድኑን የፕሮፖጋንዳ መልዕክት ፎቶ በድረ ገፃቸው ላይ ለጥፈዋል።

ባለፈው አርብ በቅዱስ ሳሙዔል ገዳም አቅራቢያ በሁለት አውቶብሶች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ሰባት የኮፕቲክ ክርስቲያኖች ሲሞቱ ሌሎች ሰባት ሰዎች ተጎድተዋል፤ ከተጎጂዎቹ መካከልም ህፃናት ይገኙበታል።

እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ (አይ ኤስ) ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

በእነዚህ በቁጥር ትንሽ በሆኑት አክራሪ ክርስቲያኖች ላይ ከተሰነዘሩት ጥቃቶች ይሄ የቅርብ ጊዜው መሆኑ ነው።

የሟቾች የቀብር ሥነ ስርዓት የተፈፀመ ሲሆን በርካታ ሰዎች ቁጣቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።

በጥቃቱ ጎረቤቱን ያጣው የ23 ዓመቱ ሚካዔል " አሸባሪዎች ከእኛ ምንድን ነው የሚፈልጉት? ሙስሊሞችን ላይ ጥላቻ እንዲኖረን ነው የሚፈልጉት?" ሲል በምሬት ይጠይቃል።

ከሶስት ዓመት በፊት በተፈፀመ ተመሳሳይ ጥቃትም 28 ክርስቲያኖች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብፅ የሚገኝ ዋነኛ ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ በርካታ መነኮሳትም እዚያው ይኖራሉ።

ቤተክርስቲያኑ በውጭ አገር አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት አሉት።