በዕድሜ ትንሹ አፍሪካዊው ቢሊዬነር ታንዛኒያ ውስጥ መታገቱን የተመለከቱና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች ያንብቡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኢትዮጵያ
በሻሸመኔ ከተማ ሰው በመግደልና ዘቅዝቆ በመስቀል ወንጀል የተጠረጠሩ 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የከተማው ፓሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መኮንን ታደሰ እንደተናገሩት ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል በስድስቱ ላይ አቃቤ ህግ ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ አግኝቷል።
*******
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባደረገው ስብሰባ የካቢኔ አባላት ቁጥርን ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ወሰነ።
በሀገሪቷ ላይ ሰላም እንዲሰፍንና ህግም እንዲከበር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ የሰላም ሚኒስቴር እንዲቋቋም መወሰኑም ተገልጿል።
ታንዛኒያ
በእድሜ ትንሹ የ43 ዓመት አፍሪካዊ ቢሊዬነር ሞሀመድ ዴውጂ በታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም በታጠቁ ሰዎች ታገተ።
አፈናውን ማን እንደፈጸመው በማጣራት ላይ መሆናቸውና የውጪ ዜጎች እጅ ሊኖርበት እንደሚችል የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽነር ላዛሮ ማሞሳሳ ገልጸዋል።
አሜሪካ
በመጪው ህዳር በሚካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ምርጫ ላይ ፈንጂ በመጠቀም የአጥፍቶ መጥፋት ተግባር ሊፈጽም አቅዷል የተባለ ሰው በቁጥጥር ስር ዋለ።
የ56 ዓመቱ ፖል ሮዘንፊልድ 91 ኪሎግራም የሚመዝን ተቀጣጣይ ፈንጂ ለማፈንዳት አዘጋጅቶ ነበር ተብሏል።
ህንድ
ህንድ ውስጥ ብዙ የመኖሪያ መንደሮችን እያሸበረች ያለች አንዲት ነብር ለመያዝ 100 የእንስሳት ጥበቃ ባለሙያዎች ተሰማሩ።
ነዋሪዎቹ ለህይወታችን ሰግተናል፤ መንግስትም ቶሎ መፍትሄ ይስጠን እያሉ ነው።
ኬንያ
የኬንያ ብሄራዊ ቡድን እሁድ ከኢትዮጵያ አቻው በካሳራኒ ስታዲየም ለሚያደርገው ጨዋታ መግቢያ በነጻ እንደሚሆን የሃገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር አስታወቀ።
ተመልካቾችም ወደ ስታዲየሙ በመግባት ልክ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች እንዳደረጉት ብሄራዊ ቡድናቸውን እንዲያበረታቱ ጠይቋል።
ናይጄሪያ
ናይጄሪያ ውስጥ በዕድሜ ትልቅ የተባሉት ታራሚ መንግስት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ።
የ100 ዓመቱ ታራሚ ሴሌስቲን የነብስ ማጥፋት ወንጀልን በማስተባበር ተከሰው እስካሁን 18 ዓመት በእስር ቆይተዋል።
አውሮፓ
እንግሊዝ አሳሳቢ ሆኖብኛል ያለችውን ነፍስን በገዛ እጅ ማጥፋት የሚቆጣጠር ሚኒስትር ሾመች።
የሚኒስትሩ ሥራም ነፍሳቸውን በገዛ እጃቸው የሚያጠፉ ዜጎችን ቁጥር የሚቀንስበትን መንገድ መፈለግ ይሆናል።
******
የአውሮፓ ሃገራትን ካጠቃው የጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ የጠፉ ሰዎች ፍለጋው እንደቀጠለ ነው።
ስፔን ውስጥ በጎርፉ ምክንያት አስር ሰዎች ሲሞቱ፤ ሁለት ፈረንሳውያንና አንዲት ጣልያናዊት ህይወታቸው አልፏል።
ዛምቢያ
የዛምቢያ መንግስት ከ1.6 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ይሰሩ የነበሩ 80 ሰራተኞችን ከስራ አገደ።
ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ የእንግሊዝ መንግስት ምንም አይነት ድጋፍ እንደማያደርግ ካስታወቀ በኋላ ነው እርምጃው የተወሰደው።
***
አፍሪካ በወጣቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ በጣም ዝቅተኛ የሚባል ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የአለም ባንክ አስታወቀ።
ምንም እንኳን ለግማሽ የቀረበው ህዝቧ ወጣት ቢሆንም፤ አፍሪካ በትምህርት፣ጤናና ስራ ፈጠራ ደካማ ናት ተብሏል።












