እንግሊዝ የጋዜጠኛ ጀማልን ጉዳይ በዋዛ እንደማትመለከተው ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, TRT WORLD
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ደብዛው እንደጠፋ የቀረው የሳዑዲው ጋዜጠኛ ዓለምን እያነጋገረ ነው። እንግሊዝ ጉዳዩን በዋዛ እንደማትመለከተው አስታውቃለች።
የሳዑዲን ንጉሣዊ አስተዳደርን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ጀማል ካሹጊ በኢስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ አንዳንድ ከጋብቻ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ወረቀቶችን ለመፈራረም ገብቶ በዚያው ቀልጦ ቀርቷል።
ደጅ ኾና ስትጠብቀው የነበረችው ቱርካዊቷ እጮኛው ለ11 ሰዓታት ያህል በር በሩን ብትመለከትም ጀማል ከኤምባሲው ቅጥር ወደ ውጭ አልወጣም።
ጋዜጠኛ ጀማል ቆንስላው ውስጥ ከመዝለቁ በፊት ለእጮኛው ተናገረ እንደተባለው "ምናልባት የቀረሁ እንደሆነ ለቱርኩ ፕሬዚዳንት ልዩ ረዳት ስልክ ደውለሽ አሳውቂ" ብሏታል። ይህም ጀማል ኤምባሲው አደጋ ሊያደርስበት እንደሚችል ጥርጣሬ እንደነበረው አመላክቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY IMAGES
የቱርክ ባለሥልጣናት ጀማል ቆንስላው ውስጥ እንደተገደለ ይጠረጥራሉ።
የወንጀል ምርመራ ባለሞያዎችም ወደ ቆንስላው ዘልቀው ሰፊ ምርመራ ለመጀመር እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀዋል።
ሳዑዲ በበኩሏ ግድያውን አስተባብላለች። ጥቂት ጋዜጠኞችን ወደ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግም የደበቅነው ነገር የለም ስትል መሳቢያና ኮሞዲኖ ጭምር በማስጎብኘት ለማረጋገጥ ሞክራለች።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሳዑዲው አቻቸው አዲል አልጁበይር በስልክ እንደተናገሩት "ወደጅነት የጋራ እሴቶችን በማክበር ላይ መመሥረት ይኖርበታል" ብለዋል።
እንደሚባለው ጋዜጠኛው ቆንስላው ውስጥ ተገድሎ ከሆነም እንግሊዝ "ነገሩን እንዲሁ እንደዋዛ" እንደማትመለከተው አስታውቃለች።
ሪያድ እንደምትለው ከሆነ ጀማል ቆንሱላውን ለቆ ወጥቷል። ቱርክ በበኩሏ ሳዑዲን ይህንኑ የሚያረጋግጥ መረጃን እንድትሰጥ እየወተወተች ነው።
ጀማል በሳዑዲ ዕለታዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የንጉሣዊያን ቤተሰብም አማካሪ ነበር። የኋላ ኋላ ሁኔታዎች አላምር ሲሉት አገሩን ጥሎ በአሜሪካ በስደት መኖር ጀመረ። የዋሺንግተን ፖስት አምደኛ ሳለ የመሐመድ ቢን ሳልማን አስተዳደርን ክፉኛ የሚተቹ ጽሑፎችን ያትም ነበር።
በጉዳዩ ላይ ዝምታን የመረጡት ዶናልድ ትራምፕ እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሚያውቁት ተራው ሕዝብ የሚያውቀውን ያህል ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ሆኖም በነገሩ ላይ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በቅርቡ እንደሚነጋገሩበት ጠቁመዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔ ሳዑዲ ለምርመራው በሯን ክፍት እንድታደርግ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ነገሩን በአስቸኳይ ገለልተኛ ቡድን ተዋቅሮ እንዲመረመር ጠይቋል።
የሳዑዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ለቡሉምበርግ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት እርሳቸውም የጀማልን መጨረሻ ለማወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ጨምረውም "ጀማል ኤምባሲያችንን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወይም ከአንድ ሰዓት በኋላ ለቆ ወጥቷል" ብለዋል።












