ክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ የቀረበው የደፍሮኛል ውንጀላ ናይኪ እጅጉን እንዳሳሰበው ገለፀ

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

ናይኪ በእግር ኳስ ተጫዋቹ ክሪስቲያኑ ሮናልዶ ላይ የቀረበው የወሲብ ቅሌት ክስ እጅጉን እንዳሳሰበው ገለፀ። ይህ ግዙፉ የስፖርት ትጥቆች አምራች ኩባንያ ከሮናልዶ ጋር የ1 ቢሊየን ዶላር የኮንትራት ስምምነት የነበረው ሲሆን አሁን ግን "ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው" እንደሆነ ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ገልጿል።

ሌላኛው የስፖርት ትጥቆች አምራች ኢኤ ስፖርትስ ከሮናልዶ ጋር ተመሳሳይ የስራ ውል ያለው ሲሆን እርሱም ጉዳዩን በአንክሮ እየተመለከተው መሆኑን አልሸሸገም።

ናይኪ በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው "የቀረበበት ውንጀላ እጅጉን ያሳስበናል ስለዚህ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልነው ነው" ሲል ኢኤ ስፖርትስ በበኩሉ " በክርስቲያኖ ሮናልዶ ላይ የቀረበውን ዝርዝር ውንጀላ በሚገባ ተመልክተነዋል፤ ከድርጅታችን ጋር የሚሰሩ ስፖርተኞች የድርጅታችንን እሴቶች በሚጠብቅ መልኩ መንቀሳቀስ ስላለባቸው ጉዳዩን በቅርበት እያየነው ነው" ብሏል።

በሌላ ወገን ደግሞ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሚጫወትበት የጣልያኑ ስፖርት ክለብ ጁቬንቱስ ከተጫዋቹ ጎን ቆሟል።

ክለቡ በቲውተር ገፁ ላይ እንዳሰፈረው " ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሙያዊ ስነምግባሩንና ያለውን መሰጠት በሚገባ እያሳየ ነው። ይህም በጁቬንቱስ ውስጥ በሁሉም ዘንድ እንዲከበር አድርጎታል" ብለዋል።

የእግር ኳስ ቡድኑ በሐምሌ ወር ከማድሪድ በ99 ሚሊየን ፓውንድ ነው የገዛው።

የ33 ዓመቱ የእግር ኳስ ኮከብ በ2009 በላስቬጋስ ካትሪን ማዮግራ ደፈረኝ የሚል ክስ ስታቀርብ ሽምጥጥ አድርጎ ክዶ ነበር።

የ34 ዓመቷ እና ቀድሞ በመምህርነት ስራ ትተዳደር የነበረችው ካትሪን ማዮግራ፣ አሁን ጉዳዩን ወደ ህግ ፊት በድጋሚ ያመጣችው በ#ሚቱ (#Me Too) እንቅስቃሴ ተነሳስታ እንደሆነ ጠበቃዋ መግለፃቸው ይታወሳል።