የጎንደር ከተማ ሙስሊሞች ለመስቀል በዓል አደባባይን ሲያፀዱ ውለዋል

የፎቶው ባለመብት, AMM
የጎንደር ከተማ ሙስሊሞች ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች ያላቸውን አለኝታነት ለማሳየት የደመራ በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በዘመቻ አፅድተዋል።
በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉ ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ወገኖች በተለምዶ መስቀል አደባባይ የሚባለውን የከተማዋን ስፍራ በዛሬው ዕለት ለሚከበረው የደመራ በዓል ትናንት በዋዜማው ምቹ እንደደረጉ እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
«ክርስቲያን ወንድሞቻችን የአረፋ በዓል በሚከበርበት ወቅት ፣በጋራ በመውጣት እኛ ሙስሊሞች የምንሰግድበት ስፍራ ማፅዳታቸውን መሰረት በማድረግ እኛም ይሄንን ተግባር ፈፅመናል፣» ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት አቶ አብዲየ ኑር የተባሉ የዘመቻው ተሳታፊ በቀጣይ ጊዜያትም መሰል ዘመቻዎችን የመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት በጅግጅጋ ከተማ በቤተ-ክርስቲያናት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ የክርስትና እና እስልምና አማኞች ተቻችለው በሚኖሩባት ጎንደር ተመሳሳይ ግጭት እንዳይፈጠር የሰጉና ውጥረቱን በሰናይ ግብር ለመመከት የወጠኑ ወጣቶች በጋራ በእስልምና ዕምነት በዓላት ወቅት የሚሰገድበትን ስታዲየም ሲያፀዱ የሚያሳይ መስል ከዚህ ቀደም በማህበራዊ ገፆች ዘንድ መሰራጨቱ ይታወሳል።
እኒህን ወጣቶች ከአስተባበሩት መካከል አንዱ የሆነው ወጣት ይሁኔ ዳኘው በዛሬው ዘመቻ ውስጥም ተሳታፊ ነበር።
«እንደምታውቁት ጎንደር የቱሪዝም መዳረሻ ናት።የሚጎበኙን ሰዎች (በሃይማኖታዊ ግጭቶች ሰበብ) የደህነነት ስጋት እንዲሰማቸው አንፈልግም።ክርስቲያኑ የመስጊዶች ጠባቂ፣ሙስሊሞች የቤተክርስቲያናት ጠባቂ የሚያደርጉ የአብሮነት ስራዎችን ለመስራት የምንፈልገውም ለዚሁ ነው» ሲል አስረድቷል።
ሽኩር መኮነን ሌላኛው በዛሬው የፅዳት ስራ ከተሰማሩ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ውሰጥ አንዱ ነው። ዘመቻውን የተቀላቀለው በሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል ያለውን ወንድማማችነት እና አብሮነት መንፈስ የሚያሳይ ተግባር ነው ብሎ በማመኑ መሆኑን ነግሮናል።
ሽኩር ወትሮም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖታዊ ጠብ ውስጥ ሊገቡ እንደማይገባ ያወሳል።
«ሲጀመር ሃይማኖት የመጣው ለሰው ልጆች ባህሪ ማስተካከያ እንጂ ልዩነት መፍጠሪያ አይደለም። ዕምነት ልዩነት መፍጠሪያ ሳይሆን፣ ነብስን መቆጣጠሪያ ነው።
ጥሩ ዕምነት ያለው ሰው ለሌላውም ጥሩውን ይመኛል፣» በማለት ከማለዳው ጀምሮ እስከ አመሻሽ በዘለቀው የፅዳት ዘመቻ የተሳተፈበት ምክንያት ለቢቢሲ አስረድቷል።












